Blogs Blogs

ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻለው በህብረት ነው

አሜን ተፈሪ

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች የመፍታት የዳበረ ልምድ ያለው ድርጅት ነው፡፡ ህልውናን የሚፈታተኑ ከባባድ ችግሮች ሲገጥሙት፤ በአስተዋይነት፣ በሩቅ አሳቢነት፣ በህዝባዊነት መርህ እየተመራ አደጋዎቹን ተራ በተራ እየተሻገረ በድል ጎዳና ተጉዟል፡፡ በመሆኑም የሐገሪቱ ልማት ስጋት የፈጠረባቸው ጠላቶች እና የኢህአዴግን ውድቀት የሚመኙ የሥልጣን ተስፈኞች ምንም ቢሉ ምን፤ ኢህአዴግ በአሁኑ ሰዓት ያጋጠሙትን ችግሮች ፈትቶ የህዳሴ ጉዞውን እንደሚቀጥል ለአፍታም ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም፡፡

 

በርግጥ፤ ከድርጅቱ ታሪክ እና ባህርይ በማይጣጣም መልኩ፤ አሁን ያጋጠመውን ችግር በመፍታት ረገድ ያሳየው ዳተኝነት እና መፋዘዝ በህዝቡ ዘንድ ‹‹ኢህአዴግ ይህን ችግሩን ይፈታው ይሆን?›› የሚል ጥርጣሬን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ህዝቡም ችግሩ ይፈታል በሚል በከፍተኛ ትዕግስት ያደረገው ጥበቃ፤ ከተለመደው በላይ የሆነ ጊዜ በመውሰዱ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሮቹ ይበልጥ ሥር እየሰደዱና እየተነባበሩ ሲከመሩ በማየቱ ሥጋት ገብቶታል፡፡ ሥጋቱም ተገቢ ሥጋት ነው፡፡ እንኳን ህዝቡ አንዳንድ የድርጅቱ ነባር አመራሮችም ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዲገፉ ያደረገ ከባድ ችግር መሆኑም የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን መላው የሐገራችን ህዝቦች በሆደ ሰፊነት ድርጅቱ ችግሮቹን እንዲያርም ዕድል ሲሰጡት፤ በረጅም የትግል ጉዞ ያካበተውን ልምዱን በመጠቀም ያጋጠመውን ችግር ለማረም የሚያስችል ሁኔታ እንደሚጥር ለመገመት ይቻላል፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት በተለየ ኃይል እና ትኩረት ችግሮቹን መፈተሽ መጀመሩን ስንመለከት፤ ኢህአዴግ ያጋጠሙትን በርካታ ችግሮች በማስወገድ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ እንደሚችል እርግጠኛ ሆነናል፡፡

 

ኢህአዴግ በርካታ ችግሮችን እየተሻገረ የመጣ ድርጅት ብቻ ሳይሆን፤ አሁንም የሚያጋጥሙትን ትክክለኛ የችግሮች አፈታት ስልት በመጠቀም ችግሮቹ እንደ ሐገር የከፋ ጉዳት ላይ ሳይጥሉን ያስወግዳቸዋል ብለን እንድንተማመን አድርጎናል፡፡ አሁን እንደ ቀድሞው ችግሮቹ ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ ለመፍታት ያልቻለበት ሁኔታ ቢከሰትም፤ ከድርጅቱ ታሪክ የምንረዳው፤ ህልውናውን የሚፈታተኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት ሰፋፊ የእርማትና የተሃድሶ ንቅናቄዎችን በማካሄድ ስር ነቀል መፍትሔ በመስጠት በድል ጎዳና የሚጓዝ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡  

 

ስለሆነም፤ ኢህአዴግ አሁን የያዘውን የእርማትና የተሃድሶ ንቅናቄ በተለመደው ቁርጠኝነት እና ትጋት መያዝ ይኖርበታል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ዕድል በዋዛ ፈዛዛ ሊያስመልጠው አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ ችግር ከተፈጠረ፤ ሐገሪቱ ወደ ኋላ የምትሄድበትን ርቀት ለመገመት ያስቸግራል፡፡

 

ኢህአዴጎች የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል በእጃቸው ላይ እንዳለ በመገንዘብ፤ ይህን ዕድል አጥብቀው ሊይዙት ይገባል፡፡ በምንም ምክንያት በእጃቸው ባለው ዕድል ቁማር ሊጫወቱ አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ መላ ህዝቡ፤ በተለይም ወጣቶች ትልቅ እገዛ ሊያደርጉለት ይገባል፡፡ ኢህአዴግም የሐገራችን ወጣቶች ሐገር የመረከብ ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዛሬም እንደ ዱሮው የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡

 

በሌላ በኩል፤ የወጣቶች የልማትና መልካም አስተዳዳር ፍላጎቶች ሊሟሉ የሚችሉት በሐገራችን ሰላምና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሁኔታ ሲኖር መሆኑን ወጣቶች እንዲረዱ ሰፊ ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ሰላምና የህግ የበላይነትን በማረጋገጡ እንቅስቃሴ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር ተጨባጭ ሥራዎችን መስራትም ይገባዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ወጣቱ ኑሮውን እንዲያማርር ያደረጉ ችግሮች እንዲፈቱለት መጠየቅ እና ጠይቆ  ያልተፈቱለት ችግሮች ሲገጥሙት በመንግስት ላይ ያሳደረውን ቅሬታ በአደባባይ ለመግለጽ ይችላል፡፡ ሆኖም ይህን ሲያደርግ አጋጣሚውን በመጠቀም ሐገሪቱን ለማፈራረስ የሚንቀሳቀሱትን አፍራሽ ኃይሎች ነቅቶ መከላከል ይኖርበታል፡፡

 

ኢህአዴግ፤ በአንድ በኩል የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የሆነውን ውስጣዊ ድክመቱን ይዋል ይደር ሳይል መፍታት እና መላውን ህብረተሰብ እና ወጣቱን የመፍትሔው አካል በማድረግ ህዝብን ያስመረሩ ችግሮች በፍጥነት እንዲወገዱ መሥራት ይኖርበታል፡፡  

 

መንግስት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ መድረኮችን መክፈት፣ በህዝቡና በመንግስት መካከል ከመቸውም ጊዜ በላይ መቀራረብና ጠንካራ ትስስር መፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የአደረጃጀትና አሰራር ለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል፤ ደግሞ ሐገሪቱን ለማተራመስ የሚደረግን ማናቸውንም አፍራሽ ድርጊት የመመከትና በመላ ሐገሪቱ ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት የሚታዩት ሁከቶች በመሠረቱ ሳይፈቱ የቆዩት ችግሮች ድምር መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም፤ የተጀመረው ዕድገትና ተስፋ ሰጭ ጉዞ ሳይሰናከል ቀጥሎ ያልተፈቱት ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር እና የሐገሪቱ ሰላም እንዳይናጋ ሳይፈቱ የቆዩ ችግሮቻችንን በፍጥነት መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን በማድረግም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በኢትዮጵያ ወዳጆች ዘንድ ስጋት የፈጠረው ችግር ከሥሩ ሊነቀል ይገባል፡፡ በዚህም ‹‹በርግጥ ችግሩ ይፈታ ይሆን?›› ከሚል ጥርጣሬ ህዝብን ማላቀቅ ይኖርበታል፡፡

 

አፍራሽ ኃይሎች ዋነኛ መሣሪያቸው ባደረጉት የማህበራዊ ሚዲያ በየደቂቃው በሚሰራጩት የፈጠራ ወሬ እና አሸባሪ መልዕክት ህዝቡ በቀላሉ እንዳይደናገር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግና መንግስት ህዝቡ እንዳይደናገር እና ትክክለኛውን ሁኔታ እንዲረዳ የማድረግ ሥራቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ እናም ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ረገድ ያለው ችግር መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል፡፡ 

 

ኢህአዴግና መንግስት፤ ‹‹በርግጥ ችግሩ ይፈታ ይሆን?›› የሚለው ጥርጣሬ እንዲወገድ የሚያደርግ እና ህዝቡን ከስጋት የሚያላቅቅ ተጨባጭ ስራ መስራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ባንድ በኩል የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የሆነው ውስጣዊ ድክመቱን ይዋል ይደር ሳይል መፍታት፤ በሌላ በኩል መላው ህብረተሰብና ወጣቱ የመፍትሄው አካላት መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡

 

ታዲያ ይህን ለማድረግ መንግስት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ መድረኮችን መክፈት፣  ይህንንም የሚያሳልጡ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ፣ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጦችን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁም በመላ ሐገሪቱ ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል፡፡

 

የተጀመረው ዕድገትና ተስፋ ሰጭ ጉዞ ሳይሰናከል ቀጥሎ፤ ያልተፈቱት ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲኖር እና የሐገሪቱ ሰላም እንዳይናጋ ለማድረግ ችግሮቻችንን በፍጥነት መፈታት ይኖርብናል፡፡ አሁን እንደ ሐገር ያጋጠመን ችግር፤ እጅግ የምሳሳለትን የሰላም፤ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግባንታ ሥራችንን በእጅጉ የሚያደናቅፍ ችግር ነው፡፡ አንዳንዶች ‹‹የምለኒየሙ ፈጣን ዕድገት›› ሲሉ የሚጠቅሱት የኢኮኖሚ ልማታችን ግለቱን እንደጠበቀ ግስጋሴውን ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሐገሪቱ በማያቋርጥ የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገባ ማድረግ የቻለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ተጠብቆ እንዲዘልቅ፤ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በጥልቀት መርምሮ እና ተረድቶ ብቁ አመራር መስጠት ያስፈልጋል፡፡

 

ዛሬ መንግስት እና መሪ ድርጅቱን እየተፈታተኗቸው ያሉት የተለያዩ ችግሮች መወገድ እና በአፍሪካ አህጉር የተነሳች ‹‹አዲሲቷ የአፍሪካ ነበር›› የሚል ስያሜ ያተረፈው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ የነበሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከድህነት አሮንቃ እንዲወጡ ማድረግ የቻለውን መስመር የሚያዛንፉ ተግዳሮቶች በአስቸኳይ እንዲወገዱ ድርጅቱ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡  

 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገው ርብርብ፤ በዓለም የድህነት ሰንጠረዥ ከግርጌ ከሚሰለፉ ሦስት ሐገሮች አንዷ የነበረችውን ሐገራችንን፤ በአዲሱ ምለኒየም ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ከሚጠቀሱ ሦስት ሐገሮች (ቻይና፣ ሚያንማር፣ ኢትዮጵያ) በሦስተኛ ደረጃ እንድትሰለፍ ማድረግ ተችሏል፡፡  የሐገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ፤ መላ የሐገራችን ህዝቦች በጊዜ የለምን መንፈስ ያደረጉትን ሰፊ እንቅስቃሴ ያስተባበረው ኢህአዴግ፤ ዳግም ጽናት እና ህዝባዊነትን ተላብሶ አደራውን መወጣት ይገባዋል፡፡

ለያዝነው አጓጊ የህዳሴ ጉዞ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መሰናክሎችን ለይቶ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ውሳኔ በማድረግ እና ለተግባራዊነቱ በመንቀሳቀስ፤ ለሐገር እና ለህዝብ አለኝታ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እና በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ክቡር የሰው ህይወት መጥፋቱ፤ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው እና የዜጎች ሐብት እና ንብረት መውደሙ ያሳዘናቸው መሆኑን የገለፁት የድርጅቱ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ እንደተናገሩት፤ ‹‹አሁን የሚታዩት እና የተለያየ መነሻ ያላቸው ችግሮች በፍጥነት ካልተወገዱ፤ እንደ ሐገር አሳሳቢ ወደሆነ ሁኔታ መግባታችን አይቀርም፡፡›› ስለዚህ ሐገራችን የተያያዘችውን የህዳሴ ጉዞ ሊያደናቅፍ የሚችለው ችግር በፍጥነት እንዲወገድ ሁሉም ዜጎች በአስተዋይ መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ትምህርትን በፍትሐዊነት ለማዳረስ እና የተማሩ ዜጎችን ቁጥር ለማሳደግ በማሰብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ በእነዚህ የሐገር ተስፋ ተደርገው በሚታዩ የትምህርት ተቋማት የተከሰቱትን አስተዳደራዊ ችግሮች እና ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ሌሎች ችግሮች በማዳመጥ መንግስት መፍትሔ ለማስቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡  

አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ‹‹በአሁኑ ወቅት በተጠቀሱት ዩኒቨርስቲዎች ተከስቶ የነበረው ችግር የክልል እና የፌዴራል መንግስታት፤ እንዲሁም የየዩኒቨርስቲዎች አመራሮች እና የየአካባቢው የመስተዳድር አካላት፤ ከተማሪዎች፣ ከሐገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች እና ከጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ…›› ተደርጓል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ከማዕከል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሄደው ከየዩኒቨርስቲ አመራሮች እና ተማሪዎች ጋር በመነጋገር ችግሮቹን ለማስወገድ ጥረት ተደርጓል፡፡ መንግስት  ሁኔታዎች ተረጋግተው መደበኛ መልካቸውን እንዲይዙ እና የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ሰፊ ጥረት ከማድረግ ባሻገር፤ አለመረጋጋቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በዚህም ውጤት ተገኝቷል፡፡

በአጠቃላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ዳግም የጸጥታ መደፍረስ ችግር እንዳይፈጠር፤ የዜጎች ህይወት ዋስትና እንዲያገኝ እና በዜጎች ሐብት እና ንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት እንዲገታ የጸጥታ ኃይሉ ጸጥታ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግላችንን የሚጎዱ፤ በጊዜ ካልተፈቱም ሐገራችንን መቋጫ የሌለው ትርምስ ውስጥ የሚከቱ፤ በመራራ ትግል የተገኘውን ብሩህ ተስፋ የሚያጨናግፉ፤ እንዲሁም ለዘመናት የቆየ የአብሮ መኖር እሴቶቻችን የሚንዱ ችግሮች በመሆናቸው መንግስት ችግሮቹን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን፤ ለ17 ቀናት በዝግ ጉባዔ ሲመክር የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ችግሮችን የሚያስወግዱ እና የኢትዮጵያን ህዝብ ለላቀ ስኬት የሚያበቁ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

በአጠቃላይ መንግስት እና ገዢው ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ህዝቡን ለምሬት የዳረጉ የአመራር ችግሮችን ለማስተካከል ጥልቅ ተሐድሶ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡም በድርጅት እና በመንግስት መዋቅሮች ያሉትን ችግሮች ከሥር መሰረታቸው ነቅሎ ለመጣል እና ራሱን ለማስተካከል የሚያስችል ሥራ ለመስራት በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ጠንከራ ግምገማ አድርጓል፡፡ ግምገማዎቹ ላይ ተመስርቶ የማያዳግም እርምጃ ወደ መውሰድ ይሸጋገራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ቻይናዎች ‹‹ለየብቻ በፍጥነት መጓዝ ይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻለው በጋራ በሚደረግ ጉዞ ነው›› ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፤ በፍጥነት መሄድም ሆነ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻለው በጋራ መሮጥ ሲቻል ብቻ መሆኑን ተገንዝበን፤ ሁላችንም ለህዝቦች አንድነት ትኩረት በመስጠት በህዳሴው ጎዳና ፈጣን እና ረጅም ጉዞ ለማድረግ እንነሳ፡፡     

የመገንጠል መብት ክፋቱ አይታየኝም

የመገንጠል መብት ክፋቱ አይታየኝም

አባ መላኩ

አንዳንዶች የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 3 በመጥቀስ ህገመንግስቱ የአገሪቱን አንድነት ለአደጋ ያጋልጣል ሲሉ ይደመጣሉ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይህ አንቀጽ በህገመንግስት ሰፈረም አልሰፈረም መገንጠል የሚፈልግ አካል ካለ የሚያግደው አንዳችም ነገር አይኖርም። ለአብነት የካታሎናዊያን ከስፔን፣ ኪዩቤክ ከካናዳ እንዲሁም ስኮታላንዶችን ከእንግሊዝ ለመነጠል ጥያቄ ከማቅረብ አላገዳቸውም። እነዚህ አገራት የመገንጠል መብትን በህገመንግስታቸው ይፋ አላደረጉትም።  እንደእኔ እንደኔ ይህ አንቀጽ በህገመንግስታችን ተጠቀሰም አልተጠቀሰም  ተገፋሁ፣ ተጨቆንኩ የሚል ብሄር ወይም ብሄረሰብ ካለ ለመገንጠል  ጥያቄ  ማቅረቡ  አይቀርም። ይህ 21ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ዜጎች መብታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁበት የመረጃ ዘመን ነው።   የኢፌዴሪ  ሕገ-መንግስት  ከመግቢያው ጀምሮ ከመገንጠል ይልቅ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጸኑ  በርካታ አንቀጦችንና ሃሳቦችን  ያካተተ ሰነድ ነው።  ለአብነት  ሕገ-መንግሥታችን መግቢያ ላይ በሕዝቦች መካከል አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ  መፍጠር የሚል  ትልቅ ሃሳብ ሰፍሮ እናገኛለን። ይህ ሃረግ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ሃሳቦችን የያዘ ነው።  

 

ሕገ-መንግስታችን  ባለፉት 27 ዓመታት  በየዘርፉ በአገራችን ለተመዘገቡ ስኬቶቻችን  መሰረት መሆኑን ማንም ሊክደው አይችልም።  የፌዴራል ስርዓታችን  በራሱ የህገ-መንግስታችን አንዱ ውጤት ነው። በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን ዋንኛ ምክንያት አገራችን  የተገበረችው የፌዴራል ስርዓት  ነው። ይህ ስርዓት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፤ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ኃይማኖታቸውን በነጻነት እንዲተገብሩ፣  በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣   ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ወዘተ መልካም ሁኔታዎችን ፈጥሯል።   እነዚህን መብቶች በተግባር ያጣጣማቸው ህዝብ አጣቸዋለሁ ብሎ እንዳይሰጋ “የመገንጠል” መብት እንዳለው  ቢያረጋግጥ  ክፋቱ አይታየኝም።   እውነት እውነቱን  እንነጋገር ከተባለ ማንም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ዳግም ወደ ቀድሞው የአፈናና የጭቆና ስርዓት ለመመለስ አይፈልግም።

 

የአገራችን የፌዴራል ስርዓት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከማስጠበቁ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንም አረጋግጧል።  የፌዴራል ስርዓታችን ህዝቦች አካባቢያቸውን እንዲያለሙ መልካም ሁኔታን በማመቻቸት ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖርም አግዟል። ዛሬ ላይ በሁሉም የክልል ከተሞቻችን አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ትላልቅ ኢቨቶችን ማስተናገድ የሚያስችል  አቅም መፍጠር ችለዋል።  ከዚህ ቀደም እዚህ ግባ የሚባል መሰረተ ልማት  ያልነበራቸው አርብቶ አደር አካባቢዎች ዛሬ ላይ የትላልቅ መሰረተ ልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠር እንግዶች የሚታደሙባቸው እንደብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በዓላት  ያሉ ኩነቶች  በታዳጋ ክልሎቻችን  በተሳካ ሁኔታ በመከበር ላይ ናቸው።   አራት  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች  በዓላት  በጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ዘንድሮ ደግሞ  በሰመራ በስኬት  ተከብሯል።   እነዚህ  በዓላት  የተከበሩት   በቀድሞ ስርዓት  እዚህ ግባ  የሚባል  መሰረተ ልማት ባልነበራቸው  አካባቢዎች  መሆኑ የሚያመላክተው  ነገር አለ።  ባለፉት 26 ዓመታት  በአገራችን እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በመዕከል ወይም በተወሰነ አካባቢ የታጠረ  አለመሆኑን   ይህ  ጥሩ ማሳያ ነው።

 

እንደእኔ እንደእኔ በአገራችን  የኃይማኖት  እክራሪነት  ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደረገው አንዱና ቀዳሚው ነገር  ህገመንግስታችን  ለኃይማኖት የሰጠው ነጻነት ይመስለኛል።  ዛሬ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። በሃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ስርዓት ተረጋግጧል። በመሆኑም ሃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር መመስረት ተችሏል። ሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮታቸውን በነጻነት የሌሎችን መብቶች አክብረው ማስተማር ኃይማኖታቸውንም በሰላማዊ መንገድ ማስፋፋት  ይችላሉ።  ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ይህን የሃይማኖት ነጻነት የሚለውን መርህ በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ባለፉት 26 ዓመታት አንዳንድ ሃይሎች  የግል ፍላጎታቸውን በኃይማኖት  ከለላ  ለማሳካት   ቢሯሯጡም  በህብረተሰቡ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም።

በአገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም  ማስፈን በመቻሉ  መንግስት ሙሉ ትኩረቱን ወደልማትና ዕድገት እንዲያደርግ አግዞታል። በተለይ  ባለፉት 15 ዓመታት አገራችን ዓለምን ያስደመመ  ባለሁለት አሃዝ  ፈጣን  ዕድገት  ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ስኬት የሕገ-መንግስታችን  ቀጥተኛ  ውጤት ነው።  መንግስት ትላልቅና አሳታፊ የሆኑ ዕቅዶችን በመንደፍና ለተግባራዊነታቸው ጥረት በማድረጉ  በየዘርፉ  ተጨባጭ ለውጦችን  ተመዝግበዋል፤ አሁን ላይ የአገራችን  የድህነት መጠን ከግማሽ በላይ በመቀነስ ወደ  ከ22 በመቶ አካባቢ እንዲወርድ ሆኗል። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ   ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ አገር አቋራጭ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የከተማ ቀላል የባቡር መስመር ዝርጋታ፣  ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎች (ከነእጥረታቸው)፣  የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም ሰፋፊ አገር አቋራጭ የመንገድ ግንባታ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አውታር ዝርጋታ ወዘተ በመካሄድ ላይ ናቸው።  መንግስት በርካታ  ቢሊዮን ዶላር ወጪዎችን በመሰረተ ልማት ማስፋፋት  ላይ በማዋሉ  ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  ኢንቨስትመንት በመሳብ ከቀዳሚዎቹ ተርታ  መሰለፍ ችላለች። በመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ የሚውል ገንዘብ ነገ የሃብት ምንጭ እንደሚሆን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግስት  የእያንዳንዷ ሰላማዊ ደቂቃ  ለአገራችን ተጨማሪ የልማት ዕድል የምትፈጥር እንደሆነች  ይገልጻታል። ይሁንና  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ   በአንዳንድ  አካባቢዎች በተቀሰቀሱት ሁከቶች  የአገራችንን ልማትና ዕድገት እየጎዱት እንደሆኑ  መመልካት የሚከብድ አይደለም። የአገራችን ህዝቦች የልማት ፍላጎት ሰፊና ትልቅ ከመሆኑ ባሻገር ፈጣንም ነው። እንኳን ካለን ላይ አፍርሰንለት(አውድመንለት)፤  እንኳን ለልማት የሚለውን ጊዜና ገንዘብ  ለነውጥና ሁከት አውለነው ይቅርና በጀመርነው  ፍጥነት እየሮጥን እንኳን የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ማሳካት አልተቻለም። የአገራችንን ዕድገትና ልማት  የተሻለ የምናደርገው በሰላማችን ላይ መደራደር ስናቆም ብቻ ነው። ይህን ስል መንግስትን መቃወም ተገቢ አይደለም ማለቴ እንዳልሆነ ሊሰመርልኝ እፈልጋለሁ። ይሁንና ተቃውሞዎች ሁሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መካሄድ እንዳለባቸው ግን  አስረግጬ መናገር እፈልጋለሁ። ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የሚደረግ ተቋውሞ  ጤነኛ  አካሄድ  አይደለም። እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ  አካሄዶች  አገራችንን ወዳልተፈለገ  መንገድ  እንደሚያመሯት  ከሶሪያ፣ ሊቢያና የመን  መማር ይመበጀን ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ  ህገመንግስት  ጭቆና ዳግም እንዳይመለስ፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ለብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መብቶች  መረጋገጥ  ዋስትና  የሚሆን  አንቀጽን አካቷል። ይህን ህጋዊ መስመርን  የሚከተል ማንኛውም መገንጠል የሚፈልግ አካል በህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በአግባብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተቀምጧል። የዚህ አንቀጽ በህገመንግስቱ  መካተት የሚያመላክተው   ህገመንግስቱ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ነው። ምክንያቱም ማንም ህጋዊውን መስመር ተከትሎ መገንጠል የሚሻ አካል  ካለ  ግጭት ውስጥ  መግባት ሳያስፈልገው  ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ  የፈለገውን  ማሳካት እንደሚችል ነው።   

በኢፌዴሪ ህገመንግስት ዜጎች በአገራቸው ውስጥ  በየትኛውም  አካባቢ በነፃነት የመዘወዋወር፣  በፈለጉበት አካባቢ የመኖር፣ ሃብት የማፍራት ህገመንግስታዊ መብትና ዋስትና  እንዳላቸው  እንዲሁም  በፈለጉ ጊዜ ከአገር ወጥተው  በፈለጉ  ጊዜ ወደ አገር  ውስጥ የመመለስ መብታቸው የተረጋገጠ  ነው።  ይሁንና  ከቅርበ ጊዜ ወዲህ  እነዚህ መብቶች  በአግባብ  እየተተገበሩ አይደለም።  በአንዳንድ አካባቢዎች  በተከሰቱ  ሁከቶች  የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት በከንቱ ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፣ ንብረቶቻቸው ተቃጠለዋል አሊያም ተዘርፈዋል።  ለዚህ ቀውስ  በዋናነት ከፍተኛ አመራሩ  በተለይ የኢህአዴግ  ስራ አስፈፃሚና  የመንግስት  ከፍተኛ  የስራ ሃላፊዎች ሃላፊነት ይሁን እንጂ  በየደረጃው ያሉ  የድርጅትና የመንግስት  የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ህብረተሰቡም  የነበራቸው ሚና ቀላል የሚባል  አይደለም። የነውጥና ሁከት ጎዳናዎች ሰፊ ሂደታቸውም አጭርና  ቀላል ይሁን እንጂ ውጤታቸው  እጅግ አስከፊና ዘግናኝ ነው። ነውጥና ሁከት  በደቂቃዎች ውስጥ  የበርካታ ንጹሃን ህይወትን ቀምቶናል፣ የበርካታዎችን አካል አጉድሏል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትንም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።  ለዓመታት የገነባናቸውን  መሃበራዊ መገልገያዎች  እንዲሁም    የግለሰቦች በህይወት ዘመናቸው  ሁሉ ያፈሯቸውን ንብረቶች  በደቂቃዎች ውስጥ አጥተዋል።  መንግስት  የህግ  የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስጠበቅ  ግዴታው ነው።   የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የማይችል መንግስት መንግስት ሊሆን አይችልም። ህብረተሰቡም  ለአገራችን ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ  ከመንግስት ጎን መቆም ተቀዳሚው ተግባሩ ሊሆን ይገባል።   

 

 

 

 

የበቀል መዳረሻው የት ይሆን?

የበቀል መዳረሻው የት ይሆን? 

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተል ከጀመረት  27 ዓመታትን አስቆጠረች።  በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ የቀንዱ አካባቢ ሠላም ደሴት መሆኗን በተግባር አሳይታለች። አገራችን የተረጋጋች ሠላም የሰፈነባት ለመሆን የበቃችው የህዝቧቿ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት መከተል በመቻሏ ብቻ ነው። በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ለአብነት የብሄር፣ የኃይማኖት፣ የማንነት፣ የአስተሳብ የሚስተዋሉባት እንዲሁም በዓለም በነውጥ ቀጠናነቱ በሚታወቀው ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምሥራቅ አፍሪካ  ቀጠና የምትገኘው ኢትዮጵያ ስኬታማ  ለመሆን የበቃችው በፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓቷ ነው። ባለፉት ሥርዓቶች የነበሩት አሃዳዊ ሥርዓቶች አገሪቱን ለምን ዳርገዋት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።   

 

እንደእኔ እንደኔ በ21ኛው ዘመን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ ራስን በራስ እንደማጥፋት የሚቆጠር ተግባር ይመስለኛል።  አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን የፌዴራል ሥርዓት ችግር እንዲገጥመው የሚደረጉ ሩጫዎች ለማንም የሚበጁ አይመስለኝም።  በኢትዮጵያ የህዝቦች  የሠላም፣ ልማትና  የዴሞክራሲ ጥያቄዎች  ምላሽ   ማግኘት  የጀመሩት  በዚህ የፌዴራል ሥርዓት ነው። ችግሮች መኖራቸው የሚካድ አይደለም፤ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ተነጋግረን ልናስተካክላቸው የምንችላቸው ናቸው። በነውጥ  የሚመጣ  ለውጥ  መዳረሻው አይታወቅም። በቀል የሠላምን መንገድ  እየዘጋ ነውጥና ሁከትን እያባባሰ ወደ ውድቀት ይመራል እንጂ መልካም ነገርን አያመጣም።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን  ዘላቂ ሠላም አስፍኖልናል፤  ልንለማ፣ ልናድግና ልንለወጥ እንደምንችል በተጨባጭ አሳይቶናል። ብዝሃነትን በአግባብና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መያዝ ከተቻለ የጥንካሬና የአንድነት ምንጭ እንደሚሆነም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ጥሩ ምሣሌ ናት።  የተለያዩ ልዩነቶችንና ፍላጎቶችን  ተቀብሎ  ዴሞክራሲያዊ  በሆነ  ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መገንባት ከተቻለ ህብረ ብሄራዊነት የልዩነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የሥርዓቱ ዋልታና ማገር በመሆን በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነትን የሚያጠናክር የአንድነት ማሰሪያ ገመድ ነው። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ከተረጋገጠ አብሮነትን የሚጠላ አካል አይኖርም። እስካሁን ያለው አብሮነትም የስኬታችን ዋነኛ መነሻም መድረሻም ነው።  

 

መንግሥት ልዩነታችንን ሊያሰፉ ህዝብን ሊያራርቁ የሚሯሯጡ ኃይላትን ከህዝቡ ጋር በመተባበር ህግ ፊት ሊገትራቸው ይገባል። የህግ የበላይነት መቼም ለድርድር መቅረብ የለበትም።  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በቅርቡ እንደተናገሩት ግጭት የቀሰቀስ ወይም ግጭት እንዲባበስ ያደረጉ ማንኛውም አካላት ከህግ ተጠያቂነት አያመልጡም። ይህን ጉዳይ  በተግባር ማየት እንፈልጋለን። ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ  ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጠባቦችና ትምክህተኞች  የህልውናችን  መሠረት የሆነውን የፌዴራል ሥርዓታችንን ለመበተን የሚያደርጉትን መሯሯጥ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈን ልንዋጋቸው ይገባል። ይህ ነገር ከመፈክር አልፎ በተግባር ልንፈጽመውም ይገባል። ለህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ የነውጠኞችንና የሴረኞችን መሰሪ አካሄድ ሊያወግዝ ይገባል።  የጥፋት ኃይሎችን ለህግ በማቅረብ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለድርድር እንደማይቀርብ ማረጋገጫ መሆን መቻል አለበት። ይህ ሲሆን ሌላውም ትምህርት ያገኛል፤ በቀጣይም ሌሎች  የጥፋት እጆችም ይሰበስባሉ።  

 

ጥቅመኞች ለህዝብና  አገር  ተቆርቋሪ  በመምሰል  አንዱን ብሄር ተጠቃህ፣ ተናቅህ፣ ወገኖችህ አለቁ ድርስላቸው ወዘተ በማለት በግጭቶች ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። በእውኑ እነዚህ ኃይሎች ለኅብረተሰቡ ተቆርቁረው ነውን? ይህን መመርመር ይገባል። አንዳንድ ሚዲያዎችም በዚህ ረገድ አካሄዳቸውን ቢያጤኑት መልካም ይመስለኛል።  የወቅቱን ነበራዊ ሁኔታዎች በቅጡ ካለመረዳት ይመስለኛል የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ስሜት ቆስቋሾች ሆነው ይታያሉ። የበቀል መንገድ  የትም አያደርስም። በበቀል አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና  ወድቀት ነው።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻል፣ መከባበርና አብሮ መኖርን ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነው። ህዝቦችን በማጋጨት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ለማንም አይበጅ። እወክለዋለሁ ለሚባለው ብሄርም  ቢሆን  በመደጋገፍና በመተሳሰብ  አብሮ በመኖር እንጂ  በመነቋቆር የሚያገኘው አንዳችም ትርፍ የለም። ባለፉት 27 ዓመታት ተቻችለንና ተከባብረን አብረን በመኖራችን በርካታ ነገሮችን አትርፈናል፤ ሰፊና አማላይ ገበያ፣ ጠንካራና አዳጊ ኢኮኖሚ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ መንግሥት፣ በሥነ ምግባር የታነፀ ህዝባዊ  የፀጥታ ኃይል ወዘተ።

 

በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በህዝቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም በፌዴራል ሥርዓታችን ጉድለት ሣቢያ የተከሰቱ ችግሮች እንዳልሆኑ ግን  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀ ውስብስብ ችግሯን መፍታት የቻለችው በዚህ የፌዴራል ሥርዓት ነው። አንዳንዶች እዚህና እዚያ የሚነሱ ትናንሽ ግጭቶችን እንደማሣያ በማቅረብ  ፌዴራል ሥርዓቱ  ድክመት አድርገው ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በተጨባጭ ያየነው ግን አገሪቱ በስኬት ጎዳና መጓዟን ነው።  ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች፣ የበርካታ ኃይማኖቶች፣ በርካታ አስተሳሰቦች፣ በርካታ ባህሎች ወዘተ  ያሉባት አገር በመሆኗ እነዚህን ልዩነቶች ሊያስተናግድ የሚችል የአስተዳደር ሥርዓት መከተል የግድ ይላታል፤ ይህ ሥርዓት ደግሞ ከነእጥረቱም ቢሆን  የፌዴራል ሥርዓት ብቻ ነው። እውነትም ይህ ሥርዓት የኢትዮጵያን ችግሮች አክሞ ባለፉት 27 ዓመታት አገሪቱን በስኬት ጎዳን እንድትረማመድ  አድርጓታል።

 

የፌዴራል ሥርዓታችን  የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች ከማረጋገጥ ባሻገር አገሪቱን በፈጣን  የምጣኔ ሀብት ለውጥ ምህዋር ውስጥ አስገብቷታል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ ተሰሚነት ባለፉት 27 ዓመታት እጅጉን  ተለውጧል፤ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም በመስፈኑ  በዓለም አቀፍ ደረጃ  የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው። ከባድ ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቢከሰትም በራስ አቅም መቋቋም ተችሏል።  ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ  በአፍሪካ ሆነ  በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን በተባበሩት መንግሥታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን መንግሥት ባከናወነው  ተግባር ነው።   ይህ የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬት አይደለምን? እነዚህን ትላልቅ  የፌዴራል ሥርዓታችን  ስኬቶች ወደ ጎን ተብለው  ለምን  ትናንሽ ነገሮችን ብቻ ለማጎን እንሽቀዳደማለን?

 

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ሠላም ዘላቂ እንዲሆን ከምታደርገው የሠላም ማስከበር ሥራ ባሻገር አገራት በምጣኔ ሀብት ጥቅም እንዲተሳሰሩ በርካታ ተግባራትን  በማከናወን ላይ ትገኛለች። ለአብነት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱ ነው።   በታዳጊ  አገር  አቅም ለመገንባት አይታሰብም የሚባለውን ይህን ፕሮጀክት አሁን ላይ  ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህስ የፌዴራል ሥርዓቱ እውን ከሆነ በኋላ የመጣ ስኬት አይደለምን? እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን  ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ሙገሳ ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ከ850 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች።  

አገሪቱ ከላይ ያነሳኋቸውን ስኬቶች  ማስመዝገብ የቻለችው ሕዝቦቿ በመከባበርና በመቻቻል አብሮ በመኖራቸው ነው። አብሮ መኖር ያስቻለን ደግሞ ልዩነቶቻችንን ማስተናገድ የስቻለን  የፌዴራል ሥርዓታችን ነው። በመሆኑም አንዳንድ ኃይሎች  በአገሪቱ  የሚስተዋሉ  የመልካም አስተዳደር ችግሮች  ሁሉ  የፌዴራል ሥርዓቱ እንከኖች አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።  አንዳንዶች ደግሞ ለህዝብና  አገር  ተቆርቋሪ  በመምሰል ትናንሽ ግጭቶችን በማጎን  እከሌ የተባለው ብሄር ሊያጠቃህ ነው፤ ተነስ፣ ለወገኖችህ  ድረስላቸው ወዘተ በማለት  በግጭቶች  ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ተመልክተናል፤ የሚሰጧቸውን መግለጫዎችም አድምጠናል። የሌለን ነገር እየፈጠሩ ብሄሮችን ማጋጨት ለማንም የማይበጅ የፖለቲካ አካሄድ ነው።  የበቀል መንገድ  የትም አያደርስም። በበቀል አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ለየትኛውም አካል ቢሆን የበቀልና የእልህ መንገድ መዳረሻው እልቂትና  ወድቀት ነውና።

 

 

የሚዲያ ግብ ሠላምና ልማት ነው

የሚዲያ ግብ ሠላምና ልማት ነው

ኢብሳ ነመራ

ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግስት፣ እንዲሁም የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስታት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸው፣ በዚህ አሰቃቂ የወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችን ለህግ እንደሚያቀርቡ አሳውቀዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ያህል ጊዜ አስቆጥሯል። በዚህ ግጭት ከሁለቱም ወገን ሰዎች ተጎድተዋል። የሁለቱም ወገን ተጎጂዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው። በሁለቱም ወገን የተጎዱት፣ ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖሩ፣ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ድህነትን ለማስወገድ በተደረገ ትግል መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላት ድህነትን መቅረፍ የጀመሩ፣ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል አምነው የተሻለ ህይወት ተስፋ ያደረባቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህ ሁኔታ ግጭቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚቆረቁር እንዲሆን ያደርገዋል።

ከዚህ ግጭት የሚያተርፍ ያለም። በዚህ የእርስ በርስ ግጭት አሸናፊ የለም። ግጭቱ በበረታና ጉዳቱ በከፋ መጠን የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሸነፈ እንደሄደ ነው የሚቆጠረው። እናም ይህን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሸናፊ የሚሆንበትን ግጭት ማስቆም ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ታዲያ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩትን የሰሞኑን ግጭት ተከትሎ በተለይ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተላለፉ ዘገባዎች ይህን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሸነፍበትን ግጭት የማቀጣጣል ዝንባሌ ባላቸው አካላት የተላለፉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በተለይ ከወደ አሜሪካ ጂግጂጋ ሄራልድ በተሰኘ ድረገጽ ላይ የተለጠፈ አንድ ዜና የኢትዮጵያውያን ጠላት ዘገባ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። The Orchestrated Massacres of Somalis in Oromia is Tantamount to an Ethnic Cleansing በሚል ርዕስ የተሰራጨው ዜና አናት ላይ ፎቶ ግራፍ ተለጥፏል። ይህ ፎቶ ግራፍ የበርካታ ሰዎች አስከሬን የታጨቀበት ጉድጓድና ጉድጓዱ አጠገብ አስከሬን የጫነ መኪና ቆሞ የሚታይበት ነው። ይህ የዜናው ምስል ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢ ያጋጠመውን ግጭት አሰቃቂ ገጽታ የማሳየት ዓላማ ያለው ነው። ይህ ምስል ግን፣ ከዚህ ከሰሞኑ ግጭት የተወሰደ አልነበረም። ከሁለት ዓመታት በፊት በቡሩንዲ አጋጥሞ ከነበረ ግጭት የተወሰደ ነው። የግጭቱን ውጤት በተሳሳተ መረጃ በማጋነን፣ ተጠቃሁ የሚለውን ወገን ለበቀል በማነሳሳት ግጭቱን ለማባባስ ሆን ተብሎ የተለጠፈ ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን ልብ በሉ።

ልብ በሉ፤ በግጭቱ ሰዎች አልሞቱም እያልኩ አይደለም። ይህን መንግስትም በይፋ ተናግሮታል። ይሁን እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሸነፍበትን ይህን ግጭት ሊያባብስ የሚችል ማንኛውንም ድርጊት መፈጸም ከህግም ከስነ ምግባርም አኳያ ጸያፍ መሆኑን ሊስተዋል  ይገባል። በተለይ መገናኛ ብዙሃን በዚህ አይነት የእርስ በርስ ግጭት ላይ እውነተኛ መረጃ እንኳን ቢኖራቸው፣ ይህን መረጃ መለቀቅ አስከፊና አደገኛ ውጤት የሚኖረው ከሆነ መልቀቅ አይኖርባቸውም። ይህን እንዲያደርጉ የሞያው ስነምግባር ያስገድዳቸዋል። የጋዜጠኝነት ወይም የመገናኛ ብዙሃን ስራ መደረሻ ሰላምን ማሰፈን፣ ልማትን ማቀላጠፍ፣ ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፉ ድርጊቶችንና እቅዶችን ማጋለጥ ወዘተ ነው። የጋዜጠኝነት ወይም የመገናኛ ብዙሃን ስራ የስነምግባር ደንብም በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው። እንግዲህ ቀደም ሲል የጠቀስኩት ሚዲያ ከዚህም አልፎ ውጤቱ አስከፊና አደገኛ የሆነ ሃሰተኛ መረጃ ነበር ያስተላለፈው። ይህ ጸያፍ ነው።

ይህ በመገናኛ ብዘሃን አካባቢ የሚታይ አዝማሚያ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ስለግጭት ምንነትና በግጭት ወቅት መገናኛ ብዙሃን ስለሚኖራቸው ድርሻ ማስታወስን አስፈላጊ ያደርገዋል።

የግጭት ምንነትና መገናኛ ብዙሃን በግጭት ወቅት ሊኖራቸውው የሚገባ ሚና ወይም የሰላም ጋዜጠኝነት ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ነው። የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ይህን ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ መተንተን አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዜጎች፣  ጋዜጠኞች፣ በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ባስገኘው እድል የተሰማቸውን ሃሳብ በፌስ ቡክ ገጽና መሰል ሚዲያዎች የሚያስተላልፉ ግለሰቦች ቆም ብለው እንዲያስቡ ማባነን ነው።

ግጭት ለሚለው እሳቤ በርካታ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የተለያየ ትርጉም ሰጥተውታል። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ በተለያዩ አካላት ከተሰጡ የግጭት ትርጉሞች ከላልሼ ያገኘሁትን ትርጉም ለመጠቀም ወድጃለሁ። ይህም ግጭት በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ቡድኖች መካከል ወይም በአንድ ቡድን አባላት መሃከል አንዱ የሌላውን አመለካከት ባለመቀበልና በመከላከል ስሜት የሚፈጠር እስከ አካላዊ ጥቃት መሰንዘር ሊዘልቅ የሚችል በባለጋራነት የመተያየት፤ የመጠላላት ሁኔታ ነው ይላል።

ግጭት እየተቀያየረ የሚሄድ ሂደትና ኡደት ያለው ሁኔታ ነው። ግጭት ከመጸነስ እስከ መክሰም የተለያየ ደረጃዎች ባሉት ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ሁኔታ ነው። የግጭት ጽንስ በሁለት ቡድኖች ወይም በአንድ ቡድን አባላት መሃከል የሚፈጠር በጥርጣሬ የመተያየት የውጥረት ሁኔታ ነው። በዚህ የውጥረት ደረጃ ወደግጭት የሚገቡ አካላት በጥርጣሬ መተያየት ይጀምራሉ። ይህ ውጥረት ረግቦ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሳይመለሱ ከቀሩና ውጥረቱ ከተባባሰ፣ ውጥረት ውስጥ ያሉ ሰዎች ጎራቸውን ወደማጥራት ይሸጋገራሉ። ሁለተኛው የግጭት ደረጃ የጎራ ማጥራት ነው። ከዚህ በኋላ ሁሉም ጎራዎች ደጋፊ ወይም አጋራቸውን በመጨመር ራሳቸውን ወገን ወደሚያጎለብቱበት የግጭት ጉልምስና ደረጃ ይሸጋገራሉ። በሁሉም ተጋጪዎች ጎራ የጎለመሰውን ግጭት እንዲሰንፍ በማድረግ ሁኔታዎችን ማርገብ ካልተቻለ አጋጣሚዎችን ጠብቆ ወደሃይል ጥቃት (violence) ደረጃ ይሸጋገራል። ይህ የግጭት የመጨረሻና አደገኛ ደረጃ ነው። ከዚህ በኋላ እንደሁኔታው ወደመርገብና መክሰም ሊመለስ ይችላል። ማናቸውንም ወደሃይል ጥቃት የተሸጋገገሩ ግጭቶች ሲመረመሩ እነዚህን ሂደቶች ያለፉ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።

በእነዚህ የግጭት እድገት ሂደት ውስጥ በማንኛውም ደረጃ ላይ ግጭቶችን የሚያበርዱ ርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል። ግጭቶችን በማርገብ ሰላምን በማስፈን ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ትልቅ ድርሻ አላቸው። ከግጭት መጸነስ እስከ የሃይል ጥቃት ያለውን ሂደት በማፋጠንና በማቀጣጣል ረገድም የዛኑ ያህል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ብዙ የተነገረለትን እ ኤ አ በ1995 ዓ.ም በሩዋንዳ የተከሰተውን የዓለማችን ዘግናኝ ግጭት ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ የቻላል። በመግቢያው ላይ እንዳነሳሁት ትክክለኛ (proper) መገናኛ ብዙሃን መድረሻቸው ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ነው። ስለሆነም የሞያውን ስነምግባር የሚያከብሩ ትክክለኛ መገናኛ ብዙሃን ግጭቶች ገሃድ መውጣት በጀመሩበት በማንኛውም ደረጃ ላይ ማምከን የሚያስችል ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

ግጭትን ከመከላከል ጋር ተያይዞ ከላይ በጠቀስነው የግጭት ሂደት ውስጥ ሊስተዋል የሚገባ አንድ የግጭት ባህሪ አለ። ይህም ግጭቶች ከውጥረት ወደ የሃይል ጥቃት እያደጉ በሄዱበት ልክ፣ አስታራቂና ሸምጋይ ድምጾች እየተደፈቁ፣ በተቃራኒው ግጭት ውስጥ የገቡት ጽንፎች ድምጾች እየጎሉ የሚሄዱ መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ የግጭቶችን ወደአደገኛ ሁኔታ መሸጋጋር ይጠቁማል። በዚህ ሂደት መገናኛ ብዙሃን በግጭቱ ትኩሳት ተጠልፈው እንደ ሁኔታው የአንዱን ወይም የሁለቱንም ጽንፎች አቋሞች በማሰራጨት ግጭት ማቀጣጠል ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ የተለመደ ነው። የውጥረትና የግጭት ዜናዎች ቀልብ ሳቢ በመሆናቸው አንባቢና ገበያ ፍለጋ  ግጭት አባባሽ ሁኔታ ውስጥ የሚገቡ መገናኛ ብዙሃነም አሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከውጤት ይልቅ ተጨባጭነት (objectivity) ላይ በማተኮር ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን የሚያቀርቡበት ሁኔታም የተለመደ ነው። እርግጥ ግጭቶችን ለማባበስ ሆን በለው የሚቋቋሙና የሚሰሩ የአንድ ወገን መገናኛ ብዙሃን አሉ። እነዚህ አደገኞች ናቸው።

በሃገራችን ያሉ የህዝብም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን አውቀውም ይሁን ባለማወቅ ግጭት አባባሽ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን የሚያመለክቱ እውነታዎች አሉ። እናም መገናኛ ብዙሃኑ ራሳቸውን  ፈትሸው እንዲቃኑ እንጠብቃለን፤ ሰላም ያስፈልገናልና።

ያም ሆነ ይህ፤ በግጭት ወቅት መገናኛ ብዙሃን የግጭቱን ባህሪና ያለበትን ደረጃ ተረደተው ግጭቶችን የሚያረግብና ሰላም የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ የሚያስችሉ የሰላም ጋዜጠኝነት ስራ የመስራት የስነምግባር ሃላፊነት አለባቸው። በተለይ ግጭቶች እየተባባሱ ሲሄዱ የጽንፎች ድምጾች እየጎሉ፣ በተቃራኒው አስታራቂና ሸምጋይ ድምጾች እየተደፈቁ ስለሚሄዱ፣ እነዚህ የሚደፈቁ የሰላም ድምጾች ላይ አተኩረው መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በአጠቃላይ አሁን በሃገራችን በተለያዩ አካበቢዎች ወደየሃይል ጥቃትነት የተሸጋገሩ ግጭቶችና ገና ወደ የሃይል ጥቃት ደረጃ ያላደጉ በውጥረት ደረጃ ላይ ያሉ ግጭቶች አሉ። የህዝብም ሆኑ የግሉ መገናኛ ብዙሃን እነዚህ ግጭቶች የሚበርዱበትና ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለመፍጠር አስበው መስራት አለባቸው። የመገናኛ ብዙሃን ግብ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንጂ ግጭትን ማባባስና ቀልብ ሳቢ የግጭ ዜና በመቸብቸብ መክበር አይደለምና።

 

 

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም እያነሣ የሚጥላት አይደለችም!

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም እያነሣ  የሚጥላት አይደለችም!

አባ መላኩ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች ተፈቃቅረውና ተከባብረው እንዲሁም ተቻችለው  የሚኖሩባት አገር ናት። ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለቀጠናው አገራት ዘላቂ  ሰላም የሚተጋ  ጠንካራ መንግስት ያላት  አገር ናት።  አንዳንድ ቅን አስተሳሰብ ያላቸው ወይም የዋህ  ዜጎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በሚስተዋሉ  የትምክህትና ጥበት ሃይሎች አካሄድ አገር የምትፈርስ ህዝብ እርስ በርሱ  የሚጫረስ መስሏቸው ስጋት ተስምቷቸዋል። ይህ አስተሳሰብ ክፋት አለው ብዬ አላስብም። ስጋቱም ምክንያታዊ አይደለም ብዬ መከራከር አልፈልግም። ይሁንና ኢትዮጵያ   ማንም  ተነስቶ ዕለቱን የሚያፈርሳት፣ የተውገረገረች  አገር እንዳልሆነች ግን በዕርግጠኝነት መናገር  ይቻላል። ህብረተሰባችን ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር ያለው ሃይማኖተኛ በርካታ የጋራ እሴቶች  ያሉት ህዝብ ነው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ  በህዝቦች ደምና አጥንት የተገነባች ህገመንግስታዊ አገር ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናስተውላቸው  ምክንያታቸው በርካታ የሆኑ  ችግሮች  አሉ። መንግስትም በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት  ችግሮች መኖራቸውን ተቀብሎ ለችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ የሚያደርገው ጥረት እንዳለ እንመለከታለን።  የአገራችንን ችግሮች ጠለቅ ብለን ብንመረምራቸው የበርካታዎቹ ችግሮች  ምንጫቸው የግል ጥቅም ፍለጋ (ኪራይ ሰብሳቢነት) ነው።  የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫ ከሆኑ ነገሮች መካካል ዋንኞቹ  የጥበትና ትምክህት አስተሳሰብና ተግባር ነው።

ጠባቦችና ትምክህተኞች  የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ስኬት አይፈልጉም። የእነዚህ ሃይሎች መደበቂያ ሃይማኖትና ብሄር ነው።  ለእነዚህ የጥፋት  ሃይሎች  የህዝቦች አብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት አይታያቸውም።  የጥበትና ትምክህት  ሃይሎች  ዓላማቸውን ለማሳካት  ሁሌም  ነውጥና ሁከትን  ይመርጣሉ። ነውጥና ሁከት መፍጠርና በተለይ በብሄሮች መካከል የሚደረግ ግጭት የጥፋት ሃይሎች ዋንኛ ስትራቴጂ ነው። አሁን ላይ ይህ ሃይል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው በከፍተኛ ትምህርት ላይ ነው።  ዩኒቨርሲቲዎች  ከትምህርት ተቋምነት ወደ  ነውጥና ሁከት እንዲያመሩ ወላጆች ልጆቻቸውን  ከትምህርት ገበታቸው ላይ  ነጥለው እንዲወስዱ የተለያዩ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ላይ ናቸው።

የጥበትና ትምክህት  ሃይሉ የጽንፈኛው የዳያስፖራ  ሚዲያዎችንና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን  በመጠቀም  አገር እንዳበቃላት  አድርገው የተለያዩ መረጃዎችን በመንዛት ላይ ናቸው። አሁን ላይ የጥበትና ትምክህት ሃይሉ  ግንባር ፈጥረው አገር የሚያፈርስ እጅግ መርዛማ መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቦችን ዕርስ በርስ  ለማጋጨት ተግተው በመስራት ላይ ናቸው።  ነውጠኛ ሃይሎች  ድብቅ አጀንዳቸውን ለማሳካት ትኩረት አድርገው እየሰሩ ያሉት ደግሞ  ወጣቱ ላይ ነው።  የበሬ ወለደ ታሪክ በማቀነባበር ወጣቱን  ስሜታዊ የሚያደርጉና    ለጥፋትና በቀል የሚያነሳሱ መረጃዎችን  በማሰራጨት አገር ልትፈርስ እንደሆነ በማስመሰል ህብረተሰቡ ላይ ስጋት ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ አይነት ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ለማንም የሚበጅ አይደለም። የመልካም አስተዳደር ችግሮች  በተላይ ወጣቶችን በተመለከተ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት  ሰላም ሲረጋገጥ እንጂ በአመጻና ነውጥ አይደለም።

የነውጥ ሃይሎች  የጥፋት ተልኳቸውን ትኩረት አድረገው እየሰሩ ያሉት  የብሄር  ግጭቶች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ ማድረግ ላይ  ነው። ግጭቶች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ  ከማድረግ ጎን ለጎን በመልካም አስተዳደር በማጓደል በህዝብ  ተገምግመው ከሃላፊነታቸው የተሰናበቱ  ግለሰቦችን በማስተባበር በመንግስት ላይ ዘመቻ መክፈት  እንደአንድ ዘዴ እየተጠቀመበት ነው።  እነዚህ የጥፋት ሃይሎች  በዚህ አያበቁም በመልካም አስተዳደር ችግሮች የተማረሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያየ ዘዴ  በመንግስት ላይ   ማነሳሳት ነው።  መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን አምኖ  ከህብረተሰቡ ጋር  መፍትሄዎችን በመስጠት ላይ ነው።     

መልካም አስተዳደር ማስፈን የዕለት ተግባር  አይደለም። ሁለም ችግሮች ዕለቱን አይፈቱም።  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ  መንግስት  የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። ይህ የመንግስት ጥረት ውጤታማ የሚሆነው በህዝብ ተሳትፎ  ሲታገዝ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይገባል።  በየትኛውም መስክ ለጥፋት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት አንዱ የመንግስት ተግባር መሆን ይገባል። የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና  ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል  ያስፈልጋል። ህዝቡ የነውጥና የሁከት  ጋሻጃግሬዎች  እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም እነዚህን አካላት ለህግ አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል።

መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩትን ጉድለቶች ለማስተካከልና  የህዝብን ፍላጎትን ለማሟላት  የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። እስካሁንም መልካምናም ተጨባጭ   ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው። ይሁንና አንዳንድ አካላት  ለምን  ሁሉም ነገር በአንዴ አልተስተካከለም ወይም አልተፈጸመም  በማለት ህብረተሰቡን ለነውጥና ለሁከት የሚያደርጉትን ሩጫ ማጋለጥ ተገቢ ነው። መንግስት ካቢኔን እንደገና እስከማዋቀር፣ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የሚገኙ ህግ የተላለፉ አስፈጻሚዎችና ፍጻሚዎችን ህግ ፊት የማቅረብ  እርምጃዎች ወስዷል። በመወሰድ ላይም ይገኛል።  ይሁንና አሁንም በርካታ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል።  ሁሉም ነገር ዕለቱን መፍትሄ ያገኛል ማለትም አይደለም።  ይሁንና በሂደት ነገሮች በመስተካከል ላይ ናቸው።  

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ የመንግስት ሚና ወሳኝ ቢሆንም  ካለህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ የታሰበው ዓላማ ሊሳካ አይችልም። ለመልካም አስተዳደር  መረጋገጥ ቁልፉ ጉዳይ አሰራር መዘርጋት ነው።  አንዳንድ   አካላት  የመንግስት ሹማምንቶችን ከኃላፊነት ቦታቸው በማንሳት ወይም በማሰር መልካም አስተዳደርን የሚረጋገጥ መስሏቸው ከራሳቸው ፍላጎት በመነሳት እከሌ ከሃላፊነት ካለወረደ፤ እከሌ ካልታሰረ ወዘተ በማለት  መንግስት  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያደርገውን ትግል ለማኮሰስ የተለያዩ  ውዥንብሮችን  በመንዛት ላይ ናቸው።  በእርግጥ ጥፋተኛ መጠየቅ ይኖርበታል፤ ነገር ግን ተጨባጭ ማስረጃ  ባለተገኘበት ሁኔታ  ማንንም  ከህግ ፊት ማቅረብ ደግሞ የግለሰቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጋፋት ነው። ህገመንግስታዊ አካሄድም አይሆንም።  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁልፉ ነገር በማንኛውም ተቋም ውስጥ የአሰራር ስርዓት  መፍጠር፣ ተጠያቂነትን ማንገስ፣ ህብረተሰቡም አገልግሎት ለማግኘት የሚጠበቅበትን  መብትና   ግዴታ ጠንቅቆ  ተገንዝቦ መብቱን ማስከበር እንዲሁም ግዴታውን እንዲወጣ ተገቢውን ድጋፍ  ማድረግ  እንጂ ፈጻሚን በየጊዜው በመቀያየር የተፈለገውን ውጤት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም።   

በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ። አንዳንድ ግለሰቦች  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ  ሁሉንም ችግሮች ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ለማስተሳሰር የሚያደርጉት ጥረት ሊወገዝ ይገባል።  ለአገራችን የሚበጃት  ሁሉንም  ችግሮች  በየፈርጁ ብንመለከታቸውና   በጋራ ሆነን መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ  በነውጥና ሁከት መፍትሄ እናመጣለን ማለት  ለአገራችንም ለህዝባችንም የሚበጃት አይሆንም። ስሜታዊነት ህዝብ ያጋጫል፣ አገርንም ያፈርሳል።  ስሜታዊነት  ምክንያታዊ እንዳንሆን  ያደርጋል። በአገራችን የሚስተዋሉ ሁሉም ችግሮች የመልካም አስተዳደር ችግሮች አይደሉም። በመንግስት የአቅም እጦት መንገድ ያልተዘረጋላቸው ወይም ውሃና ኤሌክትሪክ  ያልቀረበላቸው  አካባቢዎች  የመልካም አስተዳደር ችግር ተደርጎ መወሰድ የለበትም። 

ለአገራችን የሚበጃት ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መሆን መቻል ይኖርብናል።  በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የፊት ለፊት ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ መድረኮችን በማድረግ ላይ ነው። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ቢሆንም፤ መነጋገርና መወያየት  የሚያስችል  ፖለቲካዊ ስርዓት  በመገንባት ላይ ነው።  ይህን መልካም ጅምር ልንጠቀምበት ይገባል። መስማማት ወይም አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ፤  ቁጭ ብሎ መነጋገር  መቻል  በራሱ የመጀመሪያውና ትልቁ መልካም  ነገር ነው። 

ባለፉት 27 ዓመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 15 ዓመታት በአገራችን በርካታ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያጎለብቱና የሚያፋጥኑ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። እየተመዘገቡ ካሉ  ስኬቶች ህብረተሰቡ በየደረጃው  ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት  እየተደረገ ነው። ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል። ይሁንና መልካም አስተዳደር በማስፈን ረገድ ያልተፈቱና ህዝቡን እያማረሩ  ያሉ በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች  መኖራቸው  ገሃድ ነው። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እያንዳንዱ ዜጋ  ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ  የመንግስት ጥረት ብቻውን ውጤታማ ሊሆን አይችልም። 

 

በሰሜን ጎንደር አካባቢ የተፈጠረውን ሁከት የፀጥታ ሀይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰሩት ስራ መቆጣጠር ተችሏል- መንግስት

በሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢ የተፈጠረውን ሁከት የፀጥታ ሀይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰሩት ስራ መቆጣጠር መቻሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት አስታውቋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዜና መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “በአካባቢው ላይ የተለያዩ የህረተሰብ ጥያቄዎችን ይዘናል በማለት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥያቄውን እንደ ምሽግ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ጠላቶች የሚሰጣቸውን መመሪያ ሲፈጽሙ ቆይተዋል” ብለዋል።

“በዚህም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ሀይል እነዚህን ሰዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚሞክርበት ሰዓት ግለሰቦቹ በማሰሪያ ትእዛዝ ላይ ተሞርክዞ የቀረበላቸውን ጥያቄ አሻፈረኝ በማለት በፖሊሶች ላይ የጥይት እሩምታ በማውረድ ለሰላማዊ ሰዎች እና ለፖሊሶች ህይወት ማለፍ ተጠያቂ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯልም” ብለዋል።

በተጨማሪም በትናንትናው እለት ህፃናትን እንደ ጋሻ በመጠቀም እና ተኩስ በመክፈት በጸጥታ ሀይሎች ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውንም አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።

የግለሰቦቹ ተግባር እናራምደዋለን ከሚሉት ወይም የህብረተሰቡ ጥያቄ ነው የሚሉትን እንቅስቃሴን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የሁከት እና የግርግር ስራ ሲሰሩ እንደነበረ አስታውቀዋል።

ይህን ተግባር በማስፋፋትም ደጋፊዎቻችን ናቸው በሚሉት ጥቂት ሰዎች አማካኝነት የጠላት አላማ ለማሳካት የሚያስችሉ በተለያዩ አካባቢዎች ግርግር እና ሁከት ለመፍጠር ጥረት አድርገዋልም ብለዋል።

እንዲሁም ችግሩ በሌሎች አካባቢዎች እንዲዛመት እና ሁከቱ እንዲባባስ የሚያስችል ስራ ለመስራት መሞከራቸውን አንስተዋል።

በተለይም በሌሎች አካባቢ ተወላጆች ላይ የብሄር ትንኮሳ በማድረግ ጉዳዩ ሌላ መልክ እንዲይዝ እና ሁከቱ ወደ ለየለት ብጥብጥ እንዲሸጋገር የሚያስችል ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደቆዩም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።

ነገር ግን ህዝቡ ከጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በሰራው ስራ እንዲሁም የክልሉ የጸጥታ ሀይል ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን በሰሩት ስራ የጥፋት ሀይሎቹ ፍላጎት በሚፈልጉት ደረጃ ስኬታማ ሊሆን እልቻለም ሲሉም ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ሁከቱ እንዳይባባስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ነዋሪው በተረጋጋ መልኩ የእለት ተእለት ተግባሩን እንዲከውን እና በዛሬው እለት የተጠናቀቀውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ያለምንም ችግር ተማሪዎች እንዲፈተኑ መደረጉንም አንስተዋል።

እንዲሁም ከጎንደር ወጣ ባሉ አካባቢዎች በተለይም በአንድ አካባቢ ላይ ይህን ሁከት ለማስፋፋት ባደረጉት ጥረት የጠፋ የሰው ህይወት እና የወደመ ንብረት አለ ያሉት አቶ ጌታቸው፥ እነዚህን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰላማዊ አጀንዳ ስም የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ እና አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የመመለስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ከትናንት በስቲያ እና ትናንት በሁከት ፈጣሪዎች አማካኝነት በተፈጠረው ሁከት እና ግርግር ሳቢያ፥ አምስት ንፁሃን ዜጎች በተባራሪ ጥይት ህይወታቸው ማለፉን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ሀይል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ላይ መግለፁ ይታወቃል።

ከዚህም በተጨማሪ ከፌደራል እና ከክልሉ የፀጥታ ሀይሎች ተጨማሪ ጉዳት መድረሱንም ነው ግብረ ሃይሉ በመግለጫው የጠቆመው።

በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ በሰላማዊ ዜጎች እና የንግድ ቤቶች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥ የፌደራል እና የክልሉ የፀጥታ ሀይሎች ተጨማሪ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም ገልጿል።

የጋራ ግብረ ሀይሉ በመግለጫው በህቡዕ በመደራጀት የሽብር ተግባር በመፈፀም የህዝቡን ሰላም እንዲታወክ ከማድረግ ባለፈ እነርሱ እንደሚሉት ከማንኛውም አይነት ሰላማዊ እና ህጋዊ ጥያቄ ጋር ምንም ትስስር የሌለው ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመላክቷል።

በመግለጫው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ኤርትራ ውስጥ መሽገው ከሚገኙ የፀረ ሰላምና አሸባሪ ሀይሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና መመሪያ በመቀበል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ቁርቢ አካባቢ እንዲሁም ትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳ ደንሻና አካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን ነው የተጠቀሰው።አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 7፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሕያው ምስክር

ጀግኖች አባቶቻችን የውጭ ወራሪዎችንና ቅኝ ገዥዎችን በከፍተኛ የሃገር ፍቅር፣ ወኔ፣ ጽናትና ጀግንነት በመታገል ተደጋጋሚ ሽንፈትን እንዲጎነጩ አድርገው በመመለስ አኩሪ ታሪክ ፈጽመዋል። በዚህም ከጥንት ጀምሮ ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች፣ በጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ፋና ወጊ የሆነችና ትውልድ ሁሉ የሚኮራባትን ሃገር በደማቸው ዋዥተው በክብር አስረክበውን አልፈዋል። ለዚህም በየዘመኑ የተነሱ ቅኝ ገዥዎችንና ወራሪዎችን በጽናት በመታገል የሃገራችንን ሉአላዊነት በአስተማማኝነት አስከብረው ክብርና ሞገስ ላጎናጸፉን ጀግኖች አባቶቻችን ያለን ከበሬታ የላቀ ነው።

ኢትዮጵያ ለነጻነቷ፣ ለሉአላዊነቷና ለብሔራዊ ክብሯ መጠበቅ ታላቅ መሰዋዕትነት ከፍላ ድል ከተጎናጸፈችባቸው የወረራና የፀረ ቅኝ አገዛዝ የትግል አውዶች መካከልም በ1888 ከወራሪው የኢጣልያ ጦር ጋር በአድዋ ያደረገችው ፍልሚያና ያገኘችው አንጸባራቂ ድል በታሪክ ትልቅ ስፍራ ይዞ ይገኛል። በወቅቱ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ ጀግኖች አባቶቻችን ከጫፍ ጫፍ በመጠራራት ወራሪውን ኃይል በጋራ ለማንበርከክ የከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት በየዘመናቱ ላለው ተተኪ ትውልድ ህያው የታሪክ ምስክርነትና አርያነት ትቶ ያለፈ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው። ይህ ዘመን ተሻጋሪ የድል ቀንም በሃገራችን በየዓመቱ የሚታወስና በታላቅ ድምቀት የሚከበር እንደመሆኑ፣ ድሉ የመላ ኢትዮጵያውያን አንዱ የማንነት መገለጫና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። በመሆኑም የዘንድሮው 120ኛው ዓመት የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 /2008 "ብዝሃነትን ያከበረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን ህያው ማድረግ ችላለች!!" በሚል መሪ ቃል በድምቀት ይከበራል።

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካና በመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ውስጥ ፋና ወጊ የድል ብስራት ሆኖ ሲዘከር የኖረና ያለ አንጸባራቂና ህያው ታሪክ ነው። ይህ አኩሪ መስዋዕትነት የተከፈለበት ታላቁ የነጻነት ተጋድሎ ድሉ ከተገኘበት ዕለት ጀምሮ ታሪካዊነቱና አሻራው ሳይደበዝዝ እነሆ አሁንም ድረስ በክብር እየተዘከረ ይገኛል።

የአድዋ ጦርነትና የኢትዮጵያውያን ድል ወራሪዎችን ያሳፈረ፣ በበርካታ ታዋቂ የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ጭምር ብዙ የተባለለትና በሌላም በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ መላ ጥቁር ሕዝቦችን ለነጻነት ተጋድሎ ያነሳሳ በመሆኑ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በተለይም በወቅቱ ጥቁር ሕዝቦች በቅኝ ገዥዎች ላይ ይህን ዓይነት አንጸባራቂ ድል ሲጎናጸፉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር የወራሪውን የጣሊያንን መንግሥታዊ መዋቅር ከመሰረቱ ያናጋና ቅኝ ገዥዎችን ያሸማቀቀ ነበር። ይህ በመሆኑም ክስተቱ የመላውን ዓለም ትኩረት በእጅጉ የሳበና ያስደመመ እንደነበር በርካታ የታሪክ ድርሳናት ምስክርነታቸውን ችረውታል።

መላ የሃገራችን ሕዝቦች ሆይ!
ለቅኝ ገዥዎችና ወራሪዎች የአልምበረከክም ባይነት የትግል ወኔአችንና ቁርጠኝነታችን ዛሬም ድህነትን በመዋጋት የሃገራችንን የሕዳሴ ጉዞ የምናፋጥንበትና በመጨረሻም ስኬት የምናስመዘግብበት ሊሆን ይገባል። በመሆኑም ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን አኩሪ የጀግንነት ወኔ ተላብሶ በድህነት ላይ መዝመትና ድልን መጎናጸፍ ከፊት ለፊቱ ያለ ታሪካዊ አደራ ነው። በዚህ ረገድም ሃገራችንን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ለማረጋገጥና በዚህም አንድ ጠንካራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ ጥረት ውስጥ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቀጣይም በቁርጠኝነት በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃገራችን በፈጣን የዕድገት ግስጋሴ ውስጥ በማለፍ እያስመዘገበችው ያለውን ስኬት አጠናክረን ማስቀጠል ከቻልን በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንደምንሰለፍ የእስካሁኑ ጉዞአችን ግልጽ ማሳያ ነው። እንደ ቀደምት የጸረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎአችንና እንዳስመዘገብነው ድል ሁሉ ዛሬ ላይም በሀገራችን እየታዬ ያለው ፈጣን ዕድገትና ለውጥ የውጭውን ዓለም ትኩረት ጭምር እየሳበና ትልቅ አድናቆት እየተቸረው ይገኛል።
ቀደምት አባቶቻችን ከውጭ ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎች ጋር እንዳደረጉት የነጻነት ፍልሚያ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘመናት ከራሳቸው በወጡ ጨቋኝ ገዥዎች ተጭኖባቸው ከነበረው አፋኝና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመላቀቅ የያደረጉት መራር ትግል ፍሬ አፍርቶ በግንቦት 20 /1983 ድልን ሊጎናጸፉ ችለዋል። በዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ማህበራዊ ፍትህና ሰላም የተረጋገጠባት አዲሲቷን ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን በጋራ ትግላቸውና በከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት እውን ማደረግ ችለዋል። ብዝሃነትን በእኩልነት ያረጋገጠ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን በመሆኑም ዛሬ መላ የሃገራችን ሕዝቦች ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት በማዞር ፈጥነው ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህም ሌላ አዲስ የዕድገትና የለውጥ ታሪክ በመስራት ስኬት እያስመዘገቡ መጥተዋል። ይህ ዛሬ ላይ በተጨባጭ እየታዬ ያለው ሁለንተናዊ ዕድገትም የግንቦት 20 የትግል ውጤት በመሆኑ መላ ዜጎቻችን የሚኮሩበት ሌላው ድል ነው።

መላ የሃገራችን ሕዝቦች ከድህነት ፈጥነው ለመውጣት እያደረጉት ያለውን እልህ አስጨራሽ ትግል በማደናቀፍ የራሳቸውን ርካሽ ፍላጎት ተፈጻሚ ለማድረግ በተለያዬ ስልት የሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም ጸረ ልማትና ጸረ ሰላም ኃይሎችን በጽናት በመታገልና እኩይ ዓላማቸውን በማምከን የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ልማት ማስቀጠል የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። በመሆኑም አሁን ያለው ትውልድ የጦር ሜዳ ጀግንነታችንንና ድላችንን በልማት አርበኝነት በመድገምና ዕድገታችንን በማፋጠን ታሪክ ሰሪነቱን በተግባር እንደሚያረጋግጥና በዚህም የሃገራችንን ጥንታዊ ገናናነት እንደሚያድስ ከምን ጊዜውም በላይ ዛሬ እርግጠኞች ነን።

በመጨረሻም 120ኛውን ዓመት የአድዋ ድል በዓል ስንዘክር ልማታችንን በማፋጠን የሃገራችንን ሕዳሴና ብልጽግና እውን ለማድረግ የጋራ ቃል ኪዳናችንን በድጋሚ የምናድስበት እንደመሆኑ መላ የሃገራችን ሕዝቦች እንኳን ለ120ኛው ዓመት የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን 

— 20 Items per Page
Showing 7 results.
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ፖ ሳ ቁጥር: 1364/530
ስልክ ቁጥር: +251-115-52-81-13
:+251-115-52-81-92
ፋክስ : +251-115-52-20-60
: +251-115-54-25-87
Follow Us
Facebook
google +
youtube
twitter
© 2016 የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት