Blogs Blogs

ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻለው በህብረት ነው

አሜን ተፈሪ

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች የመፍታት የዳበረ ልምድ ያለው ድርጅት ነው፡፡ ህልውናን የሚፈታተኑ ከባባድ ችግሮች ሲገጥሙት፤ በአስተዋይነት፣ በሩቅ አሳቢነት፣ በህዝባዊነት መርህ እየተመራ አደጋዎቹን ተራ በተራ እየተሻገረ በድል ጎዳና ተጉዟል፡፡ በመሆኑም የሐገሪቱ ልማት ስጋት የፈጠረባቸው ጠላቶች እና የኢህአዴግን ውድቀት የሚመኙ የሥልጣን ተስፈኞች ምንም ቢሉ ምን፤ ኢህአዴግ በአሁኑ ሰዓት ያጋጠሙትን ችግሮች ፈትቶ የህዳሴ ጉዞውን እንደሚቀጥል ለአፍታም ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም፡፡

 

በርግጥ፤ ከድርጅቱ ታሪክ እና ባህርይ በማይጣጣም መልኩ፤ አሁን ያጋጠመውን ችግር በመፍታት ረገድ ያሳየው ዳተኝነት እና መፋዘዝ በህዝቡ ዘንድ ‹‹ኢህአዴግ ይህን ችግሩን ይፈታው ይሆን?›› የሚል ጥርጣሬን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ህዝቡም ችግሩ ይፈታል በሚል በከፍተኛ ትዕግስት ያደረገው ጥበቃ፤ ከተለመደው በላይ የሆነ ጊዜ በመውሰዱ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሮቹ ይበልጥ ሥር እየሰደዱና እየተነባበሩ ሲከመሩ በማየቱ ሥጋት ገብቶታል፡፡ ሥጋቱም ተገቢ ሥጋት ነው፡፡ እንኳን ህዝቡ አንዳንድ የድርጅቱ ነባር አመራሮችም ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዲገፉ ያደረገ ከባድ ችግር መሆኑም የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን መላው የሐገራችን ህዝቦች በሆደ ሰፊነት ድርጅቱ ችግሮቹን እንዲያርም ዕድል ሲሰጡት፤ በረጅም የትግል ጉዞ ያካበተውን ልምዱን በመጠቀም ያጋጠመውን ችግር ለማረም የሚያስችል ሁኔታ እንደሚጥር ለመገመት ይቻላል፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት በተለየ ኃይል እና ትኩረት ችግሮቹን መፈተሽ መጀመሩን ስንመለከት፤ ኢህአዴግ ያጋጠሙትን በርካታ ችግሮች በማስወገድ ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ እንደሚችል እርግጠኛ ሆነናል፡፡

 

ኢህአዴግ በርካታ ችግሮችን እየተሻገረ የመጣ ድርጅት ብቻ ሳይሆን፤ አሁንም የሚያጋጥሙትን ትክክለኛ የችግሮች አፈታት ስልት በመጠቀም ችግሮቹ እንደ ሐገር የከፋ ጉዳት ላይ ሳይጥሉን ያስወግዳቸዋል ብለን እንድንተማመን አድርጎናል፡፡ አሁን እንደ ቀድሞው ችግሮቹ ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ ለመፍታት ያልቻለበት ሁኔታ ቢከሰትም፤ ከድርጅቱ ታሪክ የምንረዳው፤ ህልውናውን የሚፈታተኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት ሰፋፊ የእርማትና የተሃድሶ ንቅናቄዎችን በማካሄድ ስር ነቀል መፍትሔ በመስጠት በድል ጎዳና የሚጓዝ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡  

 

ስለሆነም፤ ኢህአዴግ አሁን የያዘውን የእርማትና የተሃድሶ ንቅናቄ በተለመደው ቁርጠኝነት እና ትጋት መያዝ ይኖርበታል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ዕድል በዋዛ ፈዛዛ ሊያስመልጠው አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ ችግር ከተፈጠረ፤ ሐገሪቱ ወደ ኋላ የምትሄድበትን ርቀት ለመገመት ያስቸግራል፡፡

 

ኢህአዴጎች የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል በእጃቸው ላይ እንዳለ በመገንዘብ፤ ይህን ዕድል አጥብቀው ሊይዙት ይገባል፡፡ በምንም ምክንያት በእጃቸው ባለው ዕድል ቁማር ሊጫወቱ አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ መላ ህዝቡ፤ በተለይም ወጣቶች ትልቅ እገዛ ሊያደርጉለት ይገባል፡፡ ኢህአዴግም የሐገራችን ወጣቶች ሐገር የመረከብ ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዛሬም እንደ ዱሮው የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡

 

በሌላ በኩል፤ የወጣቶች የልማትና መልካም አስተዳዳር ፍላጎቶች ሊሟሉ የሚችሉት በሐገራችን ሰላምና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሁኔታ ሲኖር መሆኑን ወጣቶች እንዲረዱ ሰፊ ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ሰላምና የህግ የበላይነትን በማረጋገጡ እንቅስቃሴ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር ተጨባጭ ሥራዎችን መስራትም ይገባዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ወጣቱ ኑሮውን እንዲያማርር ያደረጉ ችግሮች እንዲፈቱለት መጠየቅ እና ጠይቆ  ያልተፈቱለት ችግሮች ሲገጥሙት በመንግስት ላይ ያሳደረውን ቅሬታ በአደባባይ ለመግለጽ ይችላል፡፡ ሆኖም ይህን ሲያደርግ አጋጣሚውን በመጠቀም ሐገሪቱን ለማፈራረስ የሚንቀሳቀሱትን አፍራሽ ኃይሎች ነቅቶ መከላከል ይኖርበታል፡፡

 

ኢህአዴግ፤ በአንድ በኩል የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የሆነውን ውስጣዊ ድክመቱን ይዋል ይደር ሳይል መፍታት እና መላውን ህብረተሰብ እና ወጣቱን የመፍትሔው አካል በማድረግ ህዝብን ያስመረሩ ችግሮች በፍጥነት እንዲወገዱ መሥራት ይኖርበታል፡፡  

 

መንግስት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ መድረኮችን መክፈት፣ በህዝቡና በመንግስት መካከል ከመቸውም ጊዜ በላይ መቀራረብና ጠንካራ ትስስር መፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የአደረጃጀትና አሰራር ለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል፤ ደግሞ ሐገሪቱን ለማተራመስ የሚደረግን ማናቸውንም አፍራሽ ድርጊት የመመከትና በመላ ሐገሪቱ ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት የሚታዩት ሁከቶች በመሠረቱ ሳይፈቱ የቆዩት ችግሮች ድምር መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም፤ የተጀመረው ዕድገትና ተስፋ ሰጭ ጉዞ ሳይሰናከል ቀጥሎ ያልተፈቱት ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር እና የሐገሪቱ ሰላም እንዳይናጋ ሳይፈቱ የቆዩ ችግሮቻችንን በፍጥነት መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን በማድረግም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በኢትዮጵያ ወዳጆች ዘንድ ስጋት የፈጠረው ችግር ከሥሩ ሊነቀል ይገባል፡፡ በዚህም ‹‹በርግጥ ችግሩ ይፈታ ይሆን?›› ከሚል ጥርጣሬ ህዝብን ማላቀቅ ይኖርበታል፡፡

 

አፍራሽ ኃይሎች ዋነኛ መሣሪያቸው ባደረጉት የማህበራዊ ሚዲያ በየደቂቃው በሚሰራጩት የፈጠራ ወሬ እና አሸባሪ መልዕክት ህዝቡ በቀላሉ እንዳይደናገር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግና መንግስት ህዝቡ እንዳይደናገር እና ትክክለኛውን ሁኔታ እንዲረዳ የማድረግ ሥራቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ እናም ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ረገድ ያለው ችግር መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል፡፡ 

 

ኢህአዴግና መንግስት፤ ‹‹በርግጥ ችግሩ ይፈታ ይሆን?›› የሚለው ጥርጣሬ እንዲወገድ የሚያደርግ እና ህዝቡን ከስጋት የሚያላቅቅ ተጨባጭ ስራ መስራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ባንድ በኩል የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የሆነው ውስጣዊ ድክመቱን ይዋል ይደር ሳይል መፍታት፤ በሌላ በኩል መላው ህብረተሰብና ወጣቱ የመፍትሄው አካላት መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡

 

ታዲያ ይህን ለማድረግ መንግስት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ መድረኮችን መክፈት፣  ይህንንም የሚያሳልጡ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ፣ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጦችን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁም በመላ ሐገሪቱ ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል፡፡

 

የተጀመረው ዕድገትና ተስፋ ሰጭ ጉዞ ሳይሰናከል ቀጥሎ፤ ያልተፈቱት ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲኖር እና የሐገሪቱ ሰላም እንዳይናጋ ለማድረግ ችግሮቻችንን በፍጥነት መፈታት ይኖርብናል፡፡ አሁን እንደ ሐገር ያጋጠመን ችግር፤ እጅግ የምሳሳለትን የሰላም፤ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግባንታ ሥራችንን በእጅጉ የሚያደናቅፍ ችግር ነው፡፡ አንዳንዶች ‹‹የምለኒየሙ ፈጣን ዕድገት›› ሲሉ የሚጠቅሱት የኢኮኖሚ ልማታችን ግለቱን እንደጠበቀ ግስጋሴውን ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሐገሪቱ በማያቋርጥ የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገባ ማድረግ የቻለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ተጠብቆ እንዲዘልቅ፤ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በጥልቀት መርምሮ እና ተረድቶ ብቁ አመራር መስጠት ያስፈልጋል፡፡

 

ዛሬ መንግስት እና መሪ ድርጅቱን እየተፈታተኗቸው ያሉት የተለያዩ ችግሮች መወገድ እና በአፍሪካ አህጉር የተነሳች ‹‹አዲሲቷ የአፍሪካ ነበር›› የሚል ስያሜ ያተረፈው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ የነበሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ከድህነት አሮንቃ እንዲወጡ ማድረግ የቻለውን መስመር የሚያዛንፉ ተግዳሮቶች በአስቸኳይ እንዲወገዱ ድርጅቱ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡  

 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገው ርብርብ፤ በዓለም የድህነት ሰንጠረዥ ከግርጌ ከሚሰለፉ ሦስት ሐገሮች አንዷ የነበረችውን ሐገራችንን፤ በአዲሱ ምለኒየም ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ከሚጠቀሱ ሦስት ሐገሮች (ቻይና፣ ሚያንማር፣ ኢትዮጵያ) በሦስተኛ ደረጃ እንድትሰለፍ ማድረግ ተችሏል፡፡  የሐገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ፤ መላ የሐገራችን ህዝቦች በጊዜ የለምን መንፈስ ያደረጉትን ሰፊ እንቅስቃሴ ያስተባበረው ኢህአዴግ፤ ዳግም ጽናት እና ህዝባዊነትን ተላብሶ አደራውን መወጣት ይገባዋል፡፡

ለያዝነው አጓጊ የህዳሴ ጉዞ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መሰናክሎችን ለይቶ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ውሳኔ በማድረግ እና ለተግባራዊነቱ በመንቀሳቀስ፤ ለሐገር እና ለህዝብ አለኝታ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እና በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ክቡር የሰው ህይወት መጥፋቱ፤ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው እና የዜጎች ሐብት እና ንብረት መውደሙ ያሳዘናቸው መሆኑን የገለፁት የድርጅቱ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ እንደተናገሩት፤ ‹‹አሁን የሚታዩት እና የተለያየ መነሻ ያላቸው ችግሮች በፍጥነት ካልተወገዱ፤ እንደ ሐገር አሳሳቢ ወደሆነ ሁኔታ መግባታችን አይቀርም፡፡›› ስለዚህ ሐገራችን የተያያዘችውን የህዳሴ ጉዞ ሊያደናቅፍ የሚችለው ችግር በፍጥነት እንዲወገድ ሁሉም ዜጎች በአስተዋይ መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ትምህርትን በፍትሐዊነት ለማዳረስ እና የተማሩ ዜጎችን ቁጥር ለማሳደግ በማሰብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተዋል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ በእነዚህ የሐገር ተስፋ ተደርገው በሚታዩ የትምህርት ተቋማት የተከሰቱትን አስተዳደራዊ ችግሮች እና ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ሌሎች ችግሮች በማዳመጥ መንግስት መፍትሔ ለማስቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡  

አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት፤ ‹‹በአሁኑ ወቅት በተጠቀሱት ዩኒቨርስቲዎች ተከስቶ የነበረው ችግር የክልል እና የፌዴራል መንግስታት፤ እንዲሁም የየዩኒቨርስቲዎች አመራሮች እና የየአካባቢው የመስተዳድር አካላት፤ ከተማሪዎች፣ ከሐገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች እና ከጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ…›› ተደርጓል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ከማዕከል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሄደው ከየዩኒቨርስቲ አመራሮች እና ተማሪዎች ጋር በመነጋገር ችግሮቹን ለማስወገድ ጥረት ተደርጓል፡፡ መንግስት  ሁኔታዎች ተረጋግተው መደበኛ መልካቸውን እንዲይዙ እና የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ሰፊ ጥረት ከማድረግ ባሻገር፤ አለመረጋጋቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በዚህም ውጤት ተገኝቷል፡፡

በአጠቃላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ዳግም የጸጥታ መደፍረስ ችግር እንዳይፈጠር፤ የዜጎች ህይወት ዋስትና እንዲያገኝ እና በዜጎች ሐብት እና ንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት እንዲገታ የጸጥታ ኃይሉ ጸጥታ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግላችንን የሚጎዱ፤ በጊዜ ካልተፈቱም ሐገራችንን መቋጫ የሌለው ትርምስ ውስጥ የሚከቱ፤ በመራራ ትግል የተገኘውን ብሩህ ተስፋ የሚያጨናግፉ፤ እንዲሁም ለዘመናት የቆየ የአብሮ መኖር እሴቶቻችን የሚንዱ ችግሮች በመሆናቸው መንግስት ችግሮቹን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን፤ ለ17 ቀናት በዝግ ጉባዔ ሲመክር የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ችግሮችን የሚያስወግዱ እና የኢትዮጵያን ህዝብ ለላቀ ስኬት የሚያበቁ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

በአጠቃላይ መንግስት እና ገዢው ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ህዝቡን ለምሬት የዳረጉ የአመራር ችግሮችን ለማስተካከል ጥልቅ ተሐድሶ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡም በድርጅት እና በመንግስት መዋቅሮች ያሉትን ችግሮች ከሥር መሰረታቸው ነቅሎ ለመጣል እና ራሱን ለማስተካከል የሚያስችል ሥራ ለመስራት በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ጠንከራ ግምገማ አድርጓል፡፡ ግምገማዎቹ ላይ ተመስርቶ የማያዳግም እርምጃ ወደ መውሰድ ይሸጋገራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ቻይናዎች ‹‹ለየብቻ በፍጥነት መጓዝ ይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻለው በጋራ በሚደረግ ጉዞ ነው›› ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፤ በፍጥነት መሄድም ሆነ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻለው በጋራ መሮጥ ሲቻል ብቻ መሆኑን ተገንዝበን፤ ሁላችንም ለህዝቦች አንድነት ትኩረት በመስጠት በህዳሴው ጎዳና ፈጣን እና ረጅም ጉዞ ለማድረግ እንነሳ፡፡     

Next
Comments
Trackback URL:

No comments yet. Be the first.
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ፖ ሳ ቁጥር: 1364/530
ስልክ ቁጥር: +251-115-52-81-13
:+251-115-52-81-92
ፋክስ : +251-115-52-20-60
: +251-115-54-25-87
Follow Us
Facebook
google +
youtube
twitter
© 2016 የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት