Blogs Blogs

የሚዲያ ግብ ሠላምና ልማት ነው

የሚዲያ ግብ ሠላምና ልማት ነው

ኢብሳ ነመራ

ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግስት፣ እንዲሁም የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስታት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸው፣ በዚህ አሰቃቂ የወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችን ለህግ እንደሚያቀርቡ አሳውቀዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ያህል ጊዜ አስቆጥሯል። በዚህ ግጭት ከሁለቱም ወገን ሰዎች ተጎድተዋል። የሁለቱም ወገን ተጎጂዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው። በሁለቱም ወገን የተጎዱት፣ ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖሩ፣ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ድህነትን ለማስወገድ በተደረገ ትግል መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላት ድህነትን መቅረፍ የጀመሩ፣ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል አምነው የተሻለ ህይወት ተስፋ ያደረባቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህ ሁኔታ ግጭቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚቆረቁር እንዲሆን ያደርገዋል።

ከዚህ ግጭት የሚያተርፍ ያለም። በዚህ የእርስ በርስ ግጭት አሸናፊ የለም። ግጭቱ በበረታና ጉዳቱ በከፋ መጠን የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሸነፈ እንደሄደ ነው የሚቆጠረው። እናም ይህን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሸናፊ የሚሆንበትን ግጭት ማስቆም ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ታዲያ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩትን የሰሞኑን ግጭት ተከትሎ በተለይ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተላለፉ ዘገባዎች ይህን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሸነፍበትን ግጭት የማቀጣጣል ዝንባሌ ባላቸው አካላት የተላለፉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በተለይ ከወደ አሜሪካ ጂግጂጋ ሄራልድ በተሰኘ ድረገጽ ላይ የተለጠፈ አንድ ዜና የኢትዮጵያውያን ጠላት ዘገባ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። The Orchestrated Massacres of Somalis in Oromia is Tantamount to an Ethnic Cleansing በሚል ርዕስ የተሰራጨው ዜና አናት ላይ ፎቶ ግራፍ ተለጥፏል። ይህ ፎቶ ግራፍ የበርካታ ሰዎች አስከሬን የታጨቀበት ጉድጓድና ጉድጓዱ አጠገብ አስከሬን የጫነ መኪና ቆሞ የሚታይበት ነው። ይህ የዜናው ምስል ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢ ያጋጠመውን ግጭት አሰቃቂ ገጽታ የማሳየት ዓላማ ያለው ነው። ይህ ምስል ግን፣ ከዚህ ከሰሞኑ ግጭት የተወሰደ አልነበረም። ከሁለት ዓመታት በፊት በቡሩንዲ አጋጥሞ ከነበረ ግጭት የተወሰደ ነው። የግጭቱን ውጤት በተሳሳተ መረጃ በማጋነን፣ ተጠቃሁ የሚለውን ወገን ለበቀል በማነሳሳት ግጭቱን ለማባባስ ሆን ተብሎ የተለጠፈ ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን ልብ በሉ።

ልብ በሉ፤ በግጭቱ ሰዎች አልሞቱም እያልኩ አይደለም። ይህን መንግስትም በይፋ ተናግሮታል። ይሁን እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሸነፍበትን ይህን ግጭት ሊያባብስ የሚችል ማንኛውንም ድርጊት መፈጸም ከህግም ከስነ ምግባርም አኳያ ጸያፍ መሆኑን ሊስተዋል  ይገባል። በተለይ መገናኛ ብዙሃን በዚህ አይነት የእርስ በርስ ግጭት ላይ እውነተኛ መረጃ እንኳን ቢኖራቸው፣ ይህን መረጃ መለቀቅ አስከፊና አደገኛ ውጤት የሚኖረው ከሆነ መልቀቅ አይኖርባቸውም። ይህን እንዲያደርጉ የሞያው ስነምግባር ያስገድዳቸዋል። የጋዜጠኝነት ወይም የመገናኛ ብዙሃን ስራ መደረሻ ሰላምን ማሰፈን፣ ልማትን ማቀላጠፍ፣ ሰላምና ልማትን የሚያደናቅፉ ድርጊቶችንና እቅዶችን ማጋለጥ ወዘተ ነው። የጋዜጠኝነት ወይም የመገናኛ ብዙሃን ስራ የስነምግባር ደንብም በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው። እንግዲህ ቀደም ሲል የጠቀስኩት ሚዲያ ከዚህም አልፎ ውጤቱ አስከፊና አደገኛ የሆነ ሃሰተኛ መረጃ ነበር ያስተላለፈው። ይህ ጸያፍ ነው።

ይህ በመገናኛ ብዘሃን አካባቢ የሚታይ አዝማሚያ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ስለግጭት ምንነትና በግጭት ወቅት መገናኛ ብዙሃን ስለሚኖራቸው ድርሻ ማስታወስን አስፈላጊ ያደርገዋል።

የግጭት ምንነትና መገናኛ ብዙሃን በግጭት ወቅት ሊኖራቸውው የሚገባ ሚና ወይም የሰላም ጋዜጠኝነት ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ነው። የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ይህን ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ መተንተን አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዜጎች፣  ጋዜጠኞች፣ በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ባስገኘው እድል የተሰማቸውን ሃሳብ በፌስ ቡክ ገጽና መሰል ሚዲያዎች የሚያስተላልፉ ግለሰቦች ቆም ብለው እንዲያስቡ ማባነን ነው።

ግጭት ለሚለው እሳቤ በርካታ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች የተለያየ ትርጉም ሰጥተውታል። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ በተለያዩ አካላት ከተሰጡ የግጭት ትርጉሞች ከላልሼ ያገኘሁትን ትርጉም ለመጠቀም ወድጃለሁ። ይህም ግጭት በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ቡድኖች መካከል ወይም በአንድ ቡድን አባላት መሃከል አንዱ የሌላውን አመለካከት ባለመቀበልና በመከላከል ስሜት የሚፈጠር እስከ አካላዊ ጥቃት መሰንዘር ሊዘልቅ የሚችል በባለጋራነት የመተያየት፤ የመጠላላት ሁኔታ ነው ይላል።

ግጭት እየተቀያየረ የሚሄድ ሂደትና ኡደት ያለው ሁኔታ ነው። ግጭት ከመጸነስ እስከ መክሰም የተለያየ ደረጃዎች ባሉት ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ሁኔታ ነው። የግጭት ጽንስ በሁለት ቡድኖች ወይም በአንድ ቡድን አባላት መሃከል የሚፈጠር በጥርጣሬ የመተያየት የውጥረት ሁኔታ ነው። በዚህ የውጥረት ደረጃ ወደግጭት የሚገቡ አካላት በጥርጣሬ መተያየት ይጀምራሉ። ይህ ውጥረት ረግቦ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሳይመለሱ ከቀሩና ውጥረቱ ከተባባሰ፣ ውጥረት ውስጥ ያሉ ሰዎች ጎራቸውን ወደማጥራት ይሸጋገራሉ። ሁለተኛው የግጭት ደረጃ የጎራ ማጥራት ነው። ከዚህ በኋላ ሁሉም ጎራዎች ደጋፊ ወይም አጋራቸውን በመጨመር ራሳቸውን ወገን ወደሚያጎለብቱበት የግጭት ጉልምስና ደረጃ ይሸጋገራሉ። በሁሉም ተጋጪዎች ጎራ የጎለመሰውን ግጭት እንዲሰንፍ በማድረግ ሁኔታዎችን ማርገብ ካልተቻለ አጋጣሚዎችን ጠብቆ ወደሃይል ጥቃት (violence) ደረጃ ይሸጋገራል። ይህ የግጭት የመጨረሻና አደገኛ ደረጃ ነው። ከዚህ በኋላ እንደሁኔታው ወደመርገብና መክሰም ሊመለስ ይችላል። ማናቸውንም ወደሃይል ጥቃት የተሸጋገገሩ ግጭቶች ሲመረመሩ እነዚህን ሂደቶች ያለፉ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።

በእነዚህ የግጭት እድገት ሂደት ውስጥ በማንኛውም ደረጃ ላይ ግጭቶችን የሚያበርዱ ርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል። ግጭቶችን በማርገብ ሰላምን በማስፈን ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ትልቅ ድርሻ አላቸው። ከግጭት መጸነስ እስከ የሃይል ጥቃት ያለውን ሂደት በማፋጠንና በማቀጣጣል ረገድም የዛኑ ያህል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ብዙ የተነገረለትን እ ኤ አ በ1995 ዓ.ም በሩዋንዳ የተከሰተውን የዓለማችን ዘግናኝ ግጭት ለዚህ ማሳያነት መጥቀስ የቻላል። በመግቢያው ላይ እንዳነሳሁት ትክክለኛ (proper) መገናኛ ብዙሃን መድረሻቸው ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ነው። ስለሆነም የሞያውን ስነምግባር የሚያከብሩ ትክክለኛ መገናኛ ብዙሃን ግጭቶች ገሃድ መውጣት በጀመሩበት በማንኛውም ደረጃ ላይ ማምከን የሚያስችል ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

ግጭትን ከመከላከል ጋር ተያይዞ ከላይ በጠቀስነው የግጭት ሂደት ውስጥ ሊስተዋል የሚገባ አንድ የግጭት ባህሪ አለ። ይህም ግጭቶች ከውጥረት ወደ የሃይል ጥቃት እያደጉ በሄዱበት ልክ፣ አስታራቂና ሸምጋይ ድምጾች እየተደፈቁ፣ በተቃራኒው ግጭት ውስጥ የገቡት ጽንፎች ድምጾች እየጎሉ የሚሄዱ መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ የግጭቶችን ወደአደገኛ ሁኔታ መሸጋጋር ይጠቁማል። በዚህ ሂደት መገናኛ ብዙሃን በግጭቱ ትኩሳት ተጠልፈው እንደ ሁኔታው የአንዱን ወይም የሁለቱንም ጽንፎች አቋሞች በማሰራጨት ግጭት ማቀጣጠል ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ የተለመደ ነው። የውጥረትና የግጭት ዜናዎች ቀልብ ሳቢ በመሆናቸው አንባቢና ገበያ ፍለጋ  ግጭት አባባሽ ሁኔታ ውስጥ የሚገቡ መገናኛ ብዙሃነም አሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከውጤት ይልቅ ተጨባጭነት (objectivity) ላይ በማተኮር ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን የሚያቀርቡበት ሁኔታም የተለመደ ነው። እርግጥ ግጭቶችን ለማባበስ ሆን በለው የሚቋቋሙና የሚሰሩ የአንድ ወገን መገናኛ ብዙሃን አሉ። እነዚህ አደገኞች ናቸው።

በሃገራችን ያሉ የህዝብም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን አውቀውም ይሁን ባለማወቅ ግጭት አባባሽ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን የሚያመለክቱ እውነታዎች አሉ። እናም መገናኛ ብዙሃኑ ራሳቸውን  ፈትሸው እንዲቃኑ እንጠብቃለን፤ ሰላም ያስፈልገናልና።

ያም ሆነ ይህ፤ በግጭት ወቅት መገናኛ ብዙሃን የግጭቱን ባህሪና ያለበትን ደረጃ ተረደተው ግጭቶችን የሚያረግብና ሰላም የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ የሚያስችሉ የሰላም ጋዜጠኝነት ስራ የመስራት የስነምግባር ሃላፊነት አለባቸው። በተለይ ግጭቶች እየተባባሱ ሲሄዱ የጽንፎች ድምጾች እየጎሉ፣ በተቃራኒው አስታራቂና ሸምጋይ ድምጾች እየተደፈቁ ስለሚሄዱ፣ እነዚህ የሚደፈቁ የሰላም ድምጾች ላይ አተኩረው መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በአጠቃላይ አሁን በሃገራችን በተለያዩ አካበቢዎች ወደየሃይል ጥቃትነት የተሸጋገሩ ግጭቶችና ገና ወደ የሃይል ጥቃት ደረጃ ያላደጉ በውጥረት ደረጃ ላይ ያሉ ግጭቶች አሉ። የህዝብም ሆኑ የግሉ መገናኛ ብዙሃን እነዚህ ግጭቶች የሚበርዱበትና ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለመፍጠር አስበው መስራት አለባቸው። የመገናኛ ብዙሃን ግብ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንጂ ግጭትን ማባባስና ቀልብ ሳቢ የግጭ ዜና በመቸብቸብ መክበር አይደለምና።

 

 

Comments
Trackback URL:

No comments yet. Be the first.
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ፖ ሳ ቁጥር: 1364/530
ስልክ ቁጥር: +251-115-52-81-13
:+251-115-52-81-92
ፋክስ : +251-115-52-20-60
: +251-115-54-25-87
Follow Us
Facebook
google +
youtube
twitter
© 2016 የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት