Blogs Blogs

በሰሜን ጎንደር አካባቢ የተፈጠረውን ሁከት የፀጥታ ሀይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰሩት ስራ መቆጣጠር ተችሏል- መንግስት

በሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢ የተፈጠረውን ሁከት የፀጥታ ሀይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰሩት ስራ መቆጣጠር መቻሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት አስታውቋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዜና መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “በአካባቢው ላይ የተለያዩ የህረተሰብ ጥያቄዎችን ይዘናል በማለት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥያቄውን እንደ ምሽግ በመጠቀም ከኢትዮጵያ ጠላቶች የሚሰጣቸውን መመሪያ ሲፈጽሙ ቆይተዋል” ብለዋል።

“በዚህም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ሀይል እነዚህን ሰዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚሞክርበት ሰዓት ግለሰቦቹ በማሰሪያ ትእዛዝ ላይ ተሞርክዞ የቀረበላቸውን ጥያቄ አሻፈረኝ በማለት በፖሊሶች ላይ የጥይት እሩምታ በማውረድ ለሰላማዊ ሰዎች እና ለፖሊሶች ህይወት ማለፍ ተጠያቂ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯልም” ብለዋል።

በተጨማሪም በትናንትናው እለት ህፃናትን እንደ ጋሻ በመጠቀም እና ተኩስ በመክፈት በጸጥታ ሀይሎች ላይ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውንም አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።

የግለሰቦቹ ተግባር እናራምደዋለን ከሚሉት ወይም የህብረተሰቡ ጥያቄ ነው የሚሉትን እንቅስቃሴን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የሁከት እና የግርግር ስራ ሲሰሩ እንደነበረ አስታውቀዋል።

ይህን ተግባር በማስፋፋትም ደጋፊዎቻችን ናቸው በሚሉት ጥቂት ሰዎች አማካኝነት የጠላት አላማ ለማሳካት የሚያስችሉ በተለያዩ አካባቢዎች ግርግር እና ሁከት ለመፍጠር ጥረት አድርገዋልም ብለዋል።

እንዲሁም ችግሩ በሌሎች አካባቢዎች እንዲዛመት እና ሁከቱ እንዲባባስ የሚያስችል ስራ ለመስራት መሞከራቸውን አንስተዋል።

በተለይም በሌሎች አካባቢ ተወላጆች ላይ የብሄር ትንኮሳ በማድረግ ጉዳዩ ሌላ መልክ እንዲይዝ እና ሁከቱ ወደ ለየለት ብጥብጥ እንዲሸጋገር የሚያስችል ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደቆዩም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።

ነገር ግን ህዝቡ ከጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በሰራው ስራ እንዲሁም የክልሉ የጸጥታ ሀይል ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን በሰሩት ስራ የጥፋት ሀይሎቹ ፍላጎት በሚፈልጉት ደረጃ ስኬታማ ሊሆን እልቻለም ሲሉም ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ሁከቱ እንዳይባባስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ነዋሪው በተረጋጋ መልኩ የእለት ተእለት ተግባሩን እንዲከውን እና በዛሬው እለት የተጠናቀቀውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ያለምንም ችግር ተማሪዎች እንዲፈተኑ መደረጉንም አንስተዋል።

እንዲሁም ከጎንደር ወጣ ባሉ አካባቢዎች በተለይም በአንድ አካባቢ ላይ ይህን ሁከት ለማስፋፋት ባደረጉት ጥረት የጠፋ የሰው ህይወት እና የወደመ ንብረት አለ ያሉት አቶ ጌታቸው፥ እነዚህን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በሰላማዊ አጀንዳ ስም የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ እና አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የመመለስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

ከትናንት በስቲያ እና ትናንት በሁከት ፈጣሪዎች አማካኝነት በተፈጠረው ሁከት እና ግርግር ሳቢያ፥ አምስት ንፁሃን ዜጎች በተባራሪ ጥይት ህይወታቸው ማለፉን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ሀይል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ላይ መግለፁ ይታወቃል።

ከዚህም በተጨማሪ ከፌደራል እና ከክልሉ የፀጥታ ሀይሎች ተጨማሪ ጉዳት መድረሱንም ነው ግብረ ሃይሉ በመግለጫው የጠቆመው።

በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ በሰላማዊ ዜጎች እና የንግድ ቤቶች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥ የፌደራል እና የክልሉ የፀጥታ ሀይሎች ተጨማሪ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም ገልጿል።

የጋራ ግብረ ሀይሉ በመግለጫው በህቡዕ በመደራጀት የሽብር ተግባር በመፈፀም የህዝቡን ሰላም እንዲታወክ ከማድረግ ባለፈ እነርሱ እንደሚሉት ከማንኛውም አይነት ሰላማዊ እና ህጋዊ ጥያቄ ጋር ምንም ትስስር የሌለው ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመላክቷል።

በመግለጫው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ኤርትራ ውስጥ መሽገው ከሚገኙ የፀረ ሰላምና አሸባሪ ሀይሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና መመሪያ በመቀበል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ቁርቢ አካባቢ እንዲሁም ትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳ ደንሻና አካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን ነው የተጠቀሰው።አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 7፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ)

የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሕያው ምስክር

ጀግኖች አባቶቻችን የውጭ ወራሪዎችንና ቅኝ ገዥዎችን በከፍተኛ የሃገር ፍቅር፣ ወኔ፣ ጽናትና ጀግንነት በመታገል ተደጋጋሚ ሽንፈትን እንዲጎነጩ አድርገው በመመለስ አኩሪ ታሪክ ፈጽመዋል። በዚህም ከጥንት ጀምሮ ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች፣ በጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ፋና ወጊ የሆነችና ትውልድ ሁሉ የሚኮራባትን ሃገር በደማቸው ዋዥተው በክብር አስረክበውን አልፈዋል። ለዚህም በየዘመኑ የተነሱ ቅኝ ገዥዎችንና ወራሪዎችን በጽናት በመታገል የሃገራችንን ሉአላዊነት በአስተማማኝነት አስከብረው ክብርና ሞገስ ላጎናጸፉን ጀግኖች አባቶቻችን ያለን ከበሬታ የላቀ ነው።

ኢትዮጵያ ለነጻነቷ፣ ለሉአላዊነቷና ለብሔራዊ ክብሯ መጠበቅ ታላቅ መሰዋዕትነት ከፍላ ድል ከተጎናጸፈችባቸው የወረራና የፀረ ቅኝ አገዛዝ የትግል አውዶች መካከልም በ1888 ከወራሪው የኢጣልያ ጦር ጋር በአድዋ ያደረገችው ፍልሚያና ያገኘችው አንጸባራቂ ድል በታሪክ ትልቅ ስፍራ ይዞ ይገኛል። በወቅቱ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ ጀግኖች አባቶቻችን ከጫፍ ጫፍ በመጠራራት ወራሪውን ኃይል በጋራ ለማንበርከክ የከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት በየዘመናቱ ላለው ተተኪ ትውልድ ህያው የታሪክ ምስክርነትና አርያነት ትቶ ያለፈ በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው። ይህ ዘመን ተሻጋሪ የድል ቀንም በሃገራችን በየዓመቱ የሚታወስና በታላቅ ድምቀት የሚከበር እንደመሆኑ፣ ድሉ የመላ ኢትዮጵያውያን አንዱ የማንነት መገለጫና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። በመሆኑም የዘንድሮው 120ኛው ዓመት የአድዋ ድል በዓል የካቲት 23 /2008 "ብዝሃነትን ያከበረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ የአድዋ ድልን ህያው ማድረግ ችላለች!!" በሚል መሪ ቃል በድምቀት ይከበራል።

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካና በመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ውስጥ ፋና ወጊ የድል ብስራት ሆኖ ሲዘከር የኖረና ያለ አንጸባራቂና ህያው ታሪክ ነው። ይህ አኩሪ መስዋዕትነት የተከፈለበት ታላቁ የነጻነት ተጋድሎ ድሉ ከተገኘበት ዕለት ጀምሮ ታሪካዊነቱና አሻራው ሳይደበዝዝ እነሆ አሁንም ድረስ በክብር እየተዘከረ ይገኛል።

የአድዋ ጦርነትና የኢትዮጵያውያን ድል ወራሪዎችን ያሳፈረ፣ በበርካታ ታዋቂ የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ጭምር ብዙ የተባለለትና በሌላም በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ መላ ጥቁር ሕዝቦችን ለነጻነት ተጋድሎ ያነሳሳ በመሆኑ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በተለይም በወቅቱ ጥቁር ሕዝቦች በቅኝ ገዥዎች ላይ ይህን ዓይነት አንጸባራቂ ድል ሲጎናጸፉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር የወራሪውን የጣሊያንን መንግሥታዊ መዋቅር ከመሰረቱ ያናጋና ቅኝ ገዥዎችን ያሸማቀቀ ነበር። ይህ በመሆኑም ክስተቱ የመላውን ዓለም ትኩረት በእጅጉ የሳበና ያስደመመ እንደነበር በርካታ የታሪክ ድርሳናት ምስክርነታቸውን ችረውታል።

መላ የሃገራችን ሕዝቦች ሆይ!
ለቅኝ ገዥዎችና ወራሪዎች የአልምበረከክም ባይነት የትግል ወኔአችንና ቁርጠኝነታችን ዛሬም ድህነትን በመዋጋት የሃገራችንን የሕዳሴ ጉዞ የምናፋጥንበትና በመጨረሻም ስኬት የምናስመዘግብበት ሊሆን ይገባል። በመሆኑም ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን አኩሪ የጀግንነት ወኔ ተላብሶ በድህነት ላይ መዝመትና ድልን መጎናጸፍ ከፊት ለፊቱ ያለ ታሪካዊ አደራ ነው። በዚህ ረገድም ሃገራችንን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ለማረጋገጥና በዚህም አንድ ጠንካራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ ጥረት ውስጥ መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቀጣይም በቁርጠኝነት በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃገራችን በፈጣን የዕድገት ግስጋሴ ውስጥ በማለፍ እያስመዘገበችው ያለውን ስኬት አጠናክረን ማስቀጠል ከቻልን በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንደምንሰለፍ የእስካሁኑ ጉዞአችን ግልጽ ማሳያ ነው። እንደ ቀደምት የጸረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎአችንና እንዳስመዘገብነው ድል ሁሉ ዛሬ ላይም በሀገራችን እየታዬ ያለው ፈጣን ዕድገትና ለውጥ የውጭውን ዓለም ትኩረት ጭምር እየሳበና ትልቅ አድናቆት እየተቸረው ይገኛል።
ቀደምት አባቶቻችን ከውጭ ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎች ጋር እንዳደረጉት የነጻነት ፍልሚያ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘመናት ከራሳቸው በወጡ ጨቋኝ ገዥዎች ተጭኖባቸው ከነበረው አፋኝና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመላቀቅ የያደረጉት መራር ትግል ፍሬ አፍርቶ በግንቦት 20 /1983 ድልን ሊጎናጸፉ ችለዋል። በዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ማህበራዊ ፍትህና ሰላም የተረጋገጠባት አዲሲቷን ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን በጋራ ትግላቸውና በከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት እውን ማደረግ ችለዋል። ብዝሃነትን በእኩልነት ያረጋገጠ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን በመሆኑም ዛሬ መላ የሃገራችን ሕዝቦች ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት በማዞር ፈጥነው ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህም ሌላ አዲስ የዕድገትና የለውጥ ታሪክ በመስራት ስኬት እያስመዘገቡ መጥተዋል። ይህ ዛሬ ላይ በተጨባጭ እየታዬ ያለው ሁለንተናዊ ዕድገትም የግንቦት 20 የትግል ውጤት በመሆኑ መላ ዜጎቻችን የሚኮሩበት ሌላው ድል ነው።

መላ የሃገራችን ሕዝቦች ከድህነት ፈጥነው ለመውጣት እያደረጉት ያለውን እልህ አስጨራሽ ትግል በማደናቀፍ የራሳቸውን ርካሽ ፍላጎት ተፈጻሚ ለማድረግ በተለያዬ ስልት የሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም ጸረ ልማትና ጸረ ሰላም ኃይሎችን በጽናት በመታገልና እኩይ ዓላማቸውን በማምከን የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ልማት ማስቀጠል የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። በመሆኑም አሁን ያለው ትውልድ የጦር ሜዳ ጀግንነታችንንና ድላችንን በልማት አርበኝነት በመድገምና ዕድገታችንን በማፋጠን ታሪክ ሰሪነቱን በተግባር እንደሚያረጋግጥና በዚህም የሃገራችንን ጥንታዊ ገናናነት እንደሚያድስ ከምን ጊዜውም በላይ ዛሬ እርግጠኞች ነን።

በመጨረሻም 120ኛውን ዓመት የአድዋ ድል በዓል ስንዘክር ልማታችንን በማፋጠን የሃገራችንን ሕዳሴና ብልጽግና እውን ለማድረግ የጋራ ቃል ኪዳናችንን በድጋሚ የምናድስበት እንደመሆኑ መላ የሃገራችን ሕዝቦች እንኳን ለ120ኛው ዓመት የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን 

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ፖ ሳ ቁጥር: 1364/530
ስልክ ቁጥር: +251-115-53-73-55
:+251-115-52-79-60
ፋክስ : +251-115-52-20-60
: +251-115-54-25-87
Follow Us
Facebook
google +
youtube
twitter
© 2016 የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት