ዜና ዜና

6ኛው የጣና ከፍተኛ የሰላምና ደህንነት ፎረም በባህር ዳር ይካሄዳል

ስድስተኛውን የጣና ከፍተኛ የሰላምና የደህንነት ፎረም ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የፎረሙ ኮሚቴ አስታወቀ።

ፎረሙ " የተፈጥሮ ሃብትን ማስተዳደር በአፍሪካ" በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያዚያ 14/2009ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል፡፡

በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የዲያስፖራ ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ፕሮቶኮል ዳይሬክተርና የአቢይ ኮሚቴው አባል አቶ አውላቸው ማስሬ እንደገለጹት ፎረሙን ለማስተናገድ አምስት የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

የመሰብሰቢያ አዳራሽና ደረጃቸውን የጠበቁ የእንግዶች ማረፊያ ሆቴሎችን የመለየት ስራዎችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ሃይልና የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዳይፈጠርም ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ አውላቸው ተናግረዋል።

የከተማዋን የቱሪዝም መስህቦች ለእንግዶቹ ለማሳየት የጽዳትና ውበት ስራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል።

ለፎረሙ ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ህዝቡ የተለመደውን የእንግዳ አቀባበል እንዲያደርግላቸው ከሆቴል ባለቤቶችና ከነዋሪዎች ጋር በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል፡፡

በፎረሙ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ የሃገራት መሪዎችና ምሁራን ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

ጣና ከፍተኛ የሰላምና የደህንነት ፎረም ወደ ጣና ፋውንዴሽን እንዲያድግ ባለፈው ዓመት መወሰኑ ይታወሳል።

ባህር ዳር ሚያዝያ 9/2009/ኢዜአ/