ዜና ዜና

210 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው 3 የቁም እንስሳት ማቆያ ኳራንቲኖች ግንባታ ተጠናቀቀ፡፡

ከ210 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሶሰት የቁም እንስሳት ማቆያ ኳራንቲኖች ግንባታ ተጠናቀቀ።

ኳራንቲኖቹን ወደ ስራ ለማስገባትም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ ለማስላክ እንደሚችሉም የእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በ2003 ዓ.ም ግንባታቸው የተጀመረው 4 ኳራንቲኖች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውንም በእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ አብርሀም ተስፋዬ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁት ኳራንቲኖች ሶስት ሲሆኑ፥ በጅግጅጋ፣ ሁመራ እና መተማ መገንባታቸውን ነው አቶ አብረሃም የሚናገሩት።

የጅግጅጋው 30 ሺህ፣ የሁመራ 6 ሺህ እንዲሁም የመተማ 6 ሺህ በግ፣ ፍየል፣ ግመል እና ዳልጋ ከብቶቸን የመያዝ አቅም ያላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።

አራተኛው ኳራንቲን አፋር ክልል ሚሌ ከ3 ወር በፊት ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ከ30 ሺህ በላይ የቁም እንሰሳትን መያዝ እንደሚችልም ሃላፊው ገልፀዋል።

እነዚህ ኳራንቲኖች የቁም እንስሳቱ የጤናን ጨምሮ የተለያዩ ክትትሎች እየተደረጉላቸው ከ21 እስከ 30 ቀን ባለው ጊዜ የሚቆዩባቸው ናቸው።

የኳራንቲኖቹ መከፈት ከዚህ ቀደም አንድ የቁም እንስሳ ይወጣበት የነበረውን ወጪ የሚቀንስ እና እንስሳቱ ለውጭ ገበያ መድረሳቸው ሲረጋገጥ ብቻ ቀጥታ ወደ ውጭ እንዲላኩ የሚያደርግ መፍትሄን የያዘ መሆኑን ነው አቶ አብርሀም የሚያነሱት።

የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማህበር አባል የሆኑት ወይዘሮ ክብሬ ሙላት በበኩላቸው፥ የኳራንቲኖች መከፈት ሀገሪቱ ማገኘት ያለባት ገቢ እንድታገኝ እና የቁም እንስሳት ላኪ ነጋዴዎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ይላሉ።

እንዲሁም የህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ያነሳሉ።

የኳራንቲኖቹ መከፈት ሀገሪቱ አሁን የምትልከተለውን የቁም እንሰሳት ቁጥር ከእጥፍ በላይ ማሳደግ እንደሚቻል የታመነበት መሆኑንም ተገልጿል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ237 ሺህ በላይ የቁም እንስሳትን በመላክ ከ64 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት የተቻለ ሲሆን፥ አሁን ስራቸው የተጠናቀቁ ማቆያ ኳራንቲኖች ስራ ሲጀምሩ ገቢውም ከዚህ የበለጠ ሊያድግ ይችላል።

  አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)