ዜና ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኤርባስ A350 ምስለ በረራ ባለቤት ሆነ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ላይ በጥቂት ሀገራት የሚገኘው እና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤርባስ "A350 XWB" ምስለ በረራ (Simulator) ባለቤት መሆኑን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የምስለ በረራ መለማመጃ መሳሪያው ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሲሆን፥ ሀይል ቆጣቢ እና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ መሆኑም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፥ ኤርባስ "A350 XWB" ምስለ በረራ ባለቤት መሆን አየር መንገዱ በአፍሪካ አቪዬሽን ቴክኖሎጂ ውስጥ ያለውን መሪነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ኤርባስ "A350 XWB" ምስለ በረራ የአየር መንገዱ የ2025 እቅድ አካል መሆኑንም ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም የB787፣ B-777፣ B737፣ B757፣ B767 እና Q400 አውሮፕናሎች ምስለ በረራ (Simulator) ባለቤት መሆኑንም አቶ ተወልደ አስታውቀዋል።

አቶ ተወልደ አያይዘውም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስልጠና አቅሙን ለማሳደግ ባለፉት 7 ዓመታት 125 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ማድረጉን ገልፀዋል።

የፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ በአፍሪካ አቪዬሽን ውስጥ የሚታየውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት እንደሚረዳ ያስታወቁ ሲሆን፥ አህጉሪቱም ብቁ የሆኑ የአቪዬሽን ባለሙያዎች እንዲኖራት ይረዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ላለፉት 50 ዓመታት በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ከሚገኙ 52 ሀገራት የመጡ አብራሪዎችን አሰልጥኗል።

የካቲት 16፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)