ዜና ዜና

ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ 9ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ጽህፈት ቤቱ አስታወቀ

በግንባታ ለሚገኘው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 9ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የቦንድ ግዥ መፈጸሙን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት አስታወቀ ።

የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር ለዋልታ እንደገለጹት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ለግድቡ ድጋፍ የሚውል 9ነጥብ6 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ ገዝቷል ።

በህብረተሰብ ተሳትፎ ለግድቡ ድጋፍ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 47 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት ሠራተኛው አስተዋጽኦ ማድረጉን የጠቆሙት ወይዘሮ ፍቅርተ ቀሪው ገቢ ከባለሃብት ፣ ከዳያስፖራና የተለያዩ የገቢ ምንጮች የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል ።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እስካሁን 877 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንና 46 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ባለፉት ስድስት ወራት መሰብሰቡን ወይዘሮ ፍቅርተ ተናግረዋል ።
ከየካቲት 20 እስከ 29 በተከበረው የቦንድ ሳምንት ብቻ ሴቶችን ባማከለ ሁኔታ በስፋት በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ 55 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ መሸጥ መቻሉን ወይዘሮ ፍቅርተ አስገንዝበዋል ።

በዘንድሮ የበጀት ዓመት በአጠቃላይ ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚውል 1ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የጠቀሱት ወይዘሮ ፍቅርተ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ዕቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረ ነው ብለዋል ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሠረት የተጣለበትን 6ኛ ዓመት በአገር ውስጥና በውጭ አገር በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ምክር ቤቱ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ወይዘሮ ፍቅርተ አመልክተዋል ።
በመጨረሻም ሁሉም ዜጋ የአንድነት መሠረት ለሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ እያደረገ ያለውን የአስተዋጽኦ ሳያቆራርጥ እንዲቀጥል ወይዘሮ ፍቅርተ ጥሪ አቅርበዋል ።

ምንጭ፡ዋልታ-መጋቢት 7/2009