ዜና ዜና

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተሰበሰበው ገንዘብ 9.6 ቢሊየን ብር ደርሷል -የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተመሰረተበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በቦንድ ግዢ፣ ልገሳና ሌሎችን ድጋፎች ጨምሮ 9.6 ቢሊየን ብር መገኘቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ፡፡

የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንዶች ክፍያ እየፈፀመ መሆኑንም ባንኩ ገልጿል፡፡

በባንኩ የኮርፖሬት ቦንድ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ካሳ እንደገለፁት ገቢው የተገኘው ከቦንድ ሽያጭ፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ፣ ከ8100 እና ከ10 ሚሊየን ብር የህዳሴ ሎተሪ፣ ከዲያስፖራው የገንዘብ ድጋፍ እና ከቦንድ ሽያጭ ሳምንት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይ የመንግስትና የግል ሰራተኛው የገባውን ቃል በመጠበቅ የቦንድ ግዢ በማከናወን ረገድ ቀዳሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በገጠር የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና በውጪ ሃገራት የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ዲያስፖራውን በማስተባበርና እንዲሁም ባለሃብቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቦንድ በመግዛት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ፍሬው እንዳሉት መንግስት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤትና ልማት ባንክ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን በየክልሉ በማዘዋወር ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግና ቦንድ እንዲገዛ እየተደረገ ነው፡፡
ህብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት ለግድቡ ግንባታ ከሚያደርገው አስተዋፅኦ ጎን ለጎን በተለይ በገጠሩ ህብረተሰብ ዘንድ የቁጠባ ባህሉ እንዲዳብር ማድረጉንም ነው የገለፁት፡፡

በሌላ በኩል በ2003/04 ተሽጠው የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሱ ቦንዶች ክፍያ እየተፈፀመ መሆኑንም አቶ አቶ ፍሬው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተቋማት በኩል በሰራተኞች ስም የተገዛን ቦንድ በመሰብሰብና ከሂሳብ ቁጥራቸው ጋር በማስተሳሰር ቦንዱን ወደገዙበት ልማት ባንክ አልያም በንግድ ባንክ ገንዘቡ ገቢ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግለሰብ የተገዛ ቦንድ የመክፈያ ጊዜው ከደረሰ ግለሰቡ ቦንዱን ለባንኩ በማስረከብ በሂሳብ ቁጥሩ ገቢ እንደሚደረግለትም ነው የገለፁት፡፡

ቦንድ ገዝተው የሂሳብ ቁጥር የሌላቸውና በጡረታ የተገለሉ ግለሰቦችም የመክፈያ ጊዜው ከደረሰ ቦንዱን በማስረከብ ቀጥታ ክፍያ እየተፈፀመላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እኤአ 2016/17 በጀት አመት ከቦንድ ሽያጭ 1.8 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ አሁን 852 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል፡፡

መጋቢት 10፣2009፣ ኢዜአ