ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም

አደጋን የመከላከል እና የመቀነስ አቅማችንን እያጎለበትን ነው!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው አደጋ አስደንጋጭ እና የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ በሃዘን የሰበረ ነው።

አደጋው መከሰቱ እንደተሰማ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በአካባቢው ተገኝተው የህይወት አድን ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ጉዳተኞች በአፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ እና በህይወት የተረፉትም በፍጥነት በጊዜያዊ መጠለያ ተሰባስበው አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። የፌዴራል ህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን አውጇል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ተጎጂዎችን ለመለየት፣ ለመደገፍና ለማቋቋም ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለጉዳቱ ተጠቂዎች እርዳታና ድጋፍ ለማድረግ ዜጎቻችን ያሳዩትን ፍላጎት ለማቀናጀትና ትርጉም ባለው መልኩ ሥራ ላይ ለማዋልም ኦፊሴላዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ የባንክ አካውንት ከፍቷል።

በአጠቃላይ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት፣ ባለሃብቶች፣ ወጣቶች እና መላው ህዝባችን አደጋው መድረሱ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ለተጎጂዎች እያሳዩት ያለው ተቆርቋሪነት፣ ትብብር እና ድጋፍ ፍጹም የሚደነቅ ነው፡፡ በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግሥት ለዚህ አኩሪ ኢትዮጵያዊ ተግባር ምሥጋናውን ያቀርባል።

መንግሥት ከሁሉ በላይ ለዘላቂ መፍትሄ ትኩረት በመስጠት የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በአንድ በኩል ከአደጋው የተረፉት ወገኖቻችን በቋሚነት ወደተረጋጋ ህይወት የሚመለሱበትን ሁኔታ እያመቻቸ ነው። በሌላ በኩል በአገራችን ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መተንበይ እና ሲከሰቱም በቅድመ ትንበያ ላይ ተመስርቶ የወገኖቻችንን ጉዳት ለመቀነስ እንዲቻል በፖሊሲ፣ በህግና በተቋም ደረጃ አቅማችንን ይበልጥ እያጎለበትን እንገኛለን።

በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግሥት ህይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በድጋሚ እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል።