ዜና ዜና

የቅዱስ ዻውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ለ71 ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረጉን አስታወቀ

የቅዱስ ዻውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ባለፉት ሰላሳ ወራት ለ71 ታካሚዎች የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማድረጉን አስታወቀ።

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናው ከአለም አቀፍ ተሞክሮ አንፃር ሲታይ ስኬታማ እንደነበርም ተገልጿል።

በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ብርሀኑ ወርቁ በአለም አቀፍ ደረጃ ዛሬ የተከበረውን የኩላሊት ቀን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

የህክምና ክፍሉ በዓመት በአማካይ ለ25 ታካሚዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማድረግ መቻሉ በምስራቅ አፍሪካ ካሉ መሰል ተቋማት የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል።

የኩላሊት ታካሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከህክምናው ባልተናነሰ ለቅድመ መከላከል ስራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር እንግዳ አበበ ተናግረዋል።

በአብዛኛው ለህክምና የሚመጡት የጉዳት መጠኑ የተባባሰባቸው ታማሚዎች በመሆናቸው የህመሙን መንስኤ ለማወቅ ሂደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ዶክተር እንግዳ ተናግረዋል ።

ይህንኑ ለማስቀረት ማንኛውም ሰው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ መክረዋል።

በሆስፒታሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው አቶ አበባው ጌታሁን "ወደ ሆስፒታሉ የመጣሁት በሰዎች ድጋፍ ነበር ከሁለት ወራት በፊት በተደረገልኝ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ጤንነቴ ተመልሶልኛል፣በተደረገልኝ ህክምና ተደስቻለሁ" ብለዋል።

የቅዱስ ዻውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ክፍል ባለፉት ሰላሳ ወራት የነበረውን አሰራር በማሻሻል የኩላሊት እጥበትን በተመጣጣኝ ክፍያና ታካሚዎች የግል ተግባራቸውን እያከናወኑ ህክምናውን የሚያገኙበት አዲስ አሰራር ሊጀምር መሆኑንም አስታውቋል።

ከውጭ ሀገራት የሚገቡና ለህክምናው የሚውሉ ቁሳቁሶች ግብይት መዘግየት ለስራው እንቅፋት እንደሆነበትና ችግሩን ለመፍታት ቁሳቁሶቹን በሀገር ውስጥ ለማምረት እቅድ መያዙም በመግለጫው ተጠቅሷል።

የኩላሊት እጥበት ህክምና ክፍል ሀላፊው ዶክተር አብዱልመኒም አህመድ ህክምናው በሌሎች አስር ሆስፒታሎች ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን በዝግጅቱ ላይ ተናግረዋል።

ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ወላይታ እንዲሁም በአዲስ አበባ በምኒሊክና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች ህክምናውን ለመስጠት መታቀዱን ገልፀዋል።

የኩላሊት ህክምና ያለበትን ደረጃ ለማሳደግ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች እንደሚከፈቱና ተሞክሮውን ለማስፋት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

የካቲት 29/2010 /ኢዜአ/