ዜና ዜና

በግማሽ ዓመቱ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ በ2010 ዓ.ም እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ለግድቡ ግንባታ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። 

ባለፉት ስድስት ወራት ከቦንድ ሽያጭ፣ እየተዘዋወረ ካለው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ፣ ከግድቡ ችቦ ከመሳሰሉ የንቅናቄ መርሃ ግብሮች ከ700 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡንም አብራርተዋል። 

ቃል የገቡ ባለሃብቶች ቃላቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ በየተሰማሩበት የሥራ መስክ የማወያየት ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው ከየካቲት 20 በኋላ ግድቡን እንዲጎበኙ ይደረጋልም ብለዋል። 

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን ሰባተኛ ዓመት አስመልክቶ በሚካሄዱ የህዝባዊ ንቅናቄ ሥራዎች ቀሪውን ገቢ ለመሰብሰብ ይሰራልም ነው ያሉት።

በዚህም የግድቡን ችቦ በሃገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በማዘዋወር ገቢ የመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ የሙዚቃ ድግስ፣ ሙዚቃዊ ድራማ፣ የሥነ ጹሁፍ ምሽቶች፣ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ እንዲሁም መኪናዎች ላይ የህዳሴ ግድብ ቦሎ እንዲለጠፍ የማድረግ ሥራዎች እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል። 

የቦንድ ሳምንት መርሃ ግብርና በ100 ከተሞች ከ500 ሺህ በላይ ሯጮችን የሚያሳትፍ ሩጫ በማዘጋጀት ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም ነው የተናገሩት፡፡

እስካሁንም ከቦንድ ሽያጭ፣ ከስጦታ፣ ከ8100 የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት፣ ከወረቀት ሎቶሪ፣ ከቲሸርት ሽያጭና ከመሳሰሉ መርሃ ግብሮች ከ10 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የተቋሙን መረጃ ኤፍቢሰ ዘግቧል ።

የካቲት 17 ፣ 2010