ዜና ዜና

ጃፓን በኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገች

ጃፓን በኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ከ600 ሚሊየን በላይ ብር ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች።

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ እንዳስታወቀው፥ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እና ለሌሎች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 628 ሚሊየን 368 ሺህ ብር በአለም አቀፍ ተቋማት በኩል ድጋፍ አድርጋለች።

ድጋፉ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ላቀደቻቸው የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት፣ ለስደተኞች ድጋፍ እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለመስጠት የሚውል ነው።

የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በማሳደግ የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸውና በራሳቸው ጥረት እንዲለወጡ ለማድረግ ጃፓን የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግም በመግለጫው ተገልጿል።

ጃፓን እስከ መጋቢት 2018 መጨረሻ ከሰሃራ በታች ላሉ ሀገሮች 145 ነጥብ 45 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ተገልጿል።

በተጨማሪም የጃፓን በአፍሪካ አህጉር መረጋጋት እንዲኖርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች ኤምባሲው ጠቁሟል።

መጋቢት 3፣ 2010 (ኢዜአ)