ዜና ዜና

ከዞኑ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ

በምእራብ ሸዋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡን የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋ ዬጃሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ገቢው የተሰበሰበው በቦንድ ግዥ ነው ።

በቦንድ ግዥው የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።

በበጀት አመቱ በቦንድ ግዥና በድጋፍ ለመሰብሰብ የታቀደውን 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አጠቃሎ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

በአምቦ ከተማ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ዋቆ ቱራ በሰጡት አስተያየት በዚህ ዓመት ለግድቡ ድጋፍ ለማድረግ የ25 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል ።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል ።

በከተማው የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ይታዩሽ ንጉሴ በበኩላቸው "እስካሁን ሶስት ጊዜ ቦንድ ገዝቻለሁ" ብለዋል ።

የግድቡ ግንባታ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ከዞኑ ህዝብ 67 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ መሰብሰቡ ታውቋል ።

ሚያዝያ 29/2009 /ኢዜአ/