ዜና ዜና

ለስደተኞች ድጋፍ የሚውል የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈረመ

በአዲስ አበባ ከተማ እና በሶማሌ ክልል ለሚገኙ ስደተኞች የቴክኒክ ድጋፍ የሚውል የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የጀርመን የቴክኒክ ትብብር /ጂ አይ ዜድ/፣ትምህርት ሚኒስቴርና የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ተፈራርመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን የቴክኒክ ትብብር ፕሮግራም አስተባባሪ ሚስ ኒኮላ ወርትስ እንደተናገሩት በስምምነቱ በአዲስ አበባና በሶማሌ ክልል የሚገኙ ስደተኞች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲያገኙ የተደረገ ስምምነት ነው፡፡

ስምምነቱ በሁለቱ አካባቢዎች የሚገኙ ስደተኞች ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ሙያዊ ስልጠናዎች እንዲያገኙ የሚያግዝ  ነው፡፡

በተለይም ለማሰልጠኛ ተቋማቱ የሚያገለግል ዕቃዎች አቅርቦት፣ ለአሰልጣኞች የአቅም ግንባታና የማሰልጠን ሂደቱን ማቀላጠፍ የስምምነቱ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሾመ ለማ በበኩላቸው ስምምነቱ አገሪቱ ለስደተኞች እያደረገች ያለውን ተግባር አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ከዚህ ባሻገር ስደተኞቹ ባሉበት አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተቋማቱ በሚሰጡት ስልጠና ሙያዊ ክህሎታቸው እንዲያድግ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡

በአሁኑ ወቅት ለስደተኞቹ መሰጠት የሚኖርባቸው ስልጠናዎች አይነትና የአሰጣጥ ሂደት የአዋጭነት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩ ሲሆን ከተያዘው የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት አመታት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘይኑ ጀማል ስምምነቱ በስደተኞችና በአገሪቱ ዜጎች መካከል ያለውን የግንኙነት ትስስር እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ስደተኞች አገሪቱ በያዘችው የልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡

ስደተኞቹ ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማድረግ በኩል ስምምነቱ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም እንዲሁ፡፡

በኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራና ሶማሊያ የተሰደዱ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ፡፡

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010/ኢዜአ/