ዜና ዜና

በአማራ ክልል እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ከ59 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

በአማራ ክልል እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ከ59 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቀድመው በሚዘሩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በዘንድሮው መኽርም ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት መጣል የጀመረውን ዝናብ በመጠቀም ካለፈው ወር ጀምሮ የዘር ስራው እየተከናወነ ይገኛል።

በምርት ዘመኑ እንዲለማ ከታቀደው መሬት ውስጥ እስካሁን ወደ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋው እስከ አራት ዙር የታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ59 ሺህ ሔክታር የሚበልጠው ደግሞ ቀድመው በሚዘሩ በበቆሎ፣ድንችና ገብስ መሸፈኑን አስረድተዋል።

"ቀሪውን መሬት አርሶ አደሩ በቀጣይ ወቅቱን ጠብቆ የዘር ስራውን እንዲያከናውን በየደረጃው የሚገኘው የግብርና ባለሙያ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።

ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከታቀደው አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋው እየተከፋፈለ ሲሆን ቀሪውን በተለይ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች በወቅቱ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

"በአሁኑ ወቅትም የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ክምችት ካለባቸው አካባቢዎች በማጓጓዝ ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው "ያሉት አቶ ተስፋሁን በተጨማሪም ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በቀዳሚው የምርት ዘመን በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት 95 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን ዘንድሮ ከ133 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባህርዳር ግንቦት 11/9/2009/ኢዜአ/