ዜና ዜና

ባለፉት ስምንት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከ481 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት ከ481 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ገቢውን ያገኘው ባለፉት ስምንት ወራት 137 ሺህ 417 ቶን በላይ ቡና ወደ ተለያዩ ሃገራት በመላክ መሆኑንም አስታውቋል።

የቡና ምርቱ ከ50 በላይ ወደሆኑ ሃገራት የተላከ መሆኑም ታውቋል።

የተላከው የቡና ምርት የእቅዱን 101 ነጥብ 55 መሆኑንም ገልጿል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳሬክተር እና የግብይት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሻፊ ኡመር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ዘንድሮ ወደ ውጭ የተላከው የቡና ምርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ አሳይቷል።

በመጠን በ24 ሺህ 583 ቶን እንዲሁም በገቢ ደግሞ የ47 ሚሊየን 570 ሺህ ብር ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

ሳዑድ ዓረቢያ፣ ጀርመን፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ቤልጅየም፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ሱዳን እና እንግሊዝ በቅደም ተከተል ቀዳሚ የመዳረሻ ሃገራት ናቸው።

ሚያዚያ 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)