ዜና ዜና

ለዘንድሮው የመኸር ምርት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱ ተገለጸ።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ለመኸር ምርት በቀጥታ የዘር ግብይት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን ገለፀ።

ኤጀንሲው የመኸር ምርት የዘር አቅርቦትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የቀጥታ የዘር ግብይት ዘር አምራቾች የራሳቸውን ወኪሎች በመጠቀም የዘር አቅርቦትን ለአርሶ አደሮች የሚያደርሱበት ስርዓት ሲሆን ይህ አገልግሎት ከዚህ በፊት የነበረን የተንዛዛ አሰራር በማሳጠር አርሶ አደሮች በቀጥታ ከዘር አምራቾች ጋር የሚያገናኝ መንገድ ነው።

የግብዓትና ሰብል ጥበቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ይትባረክ ሰመዓኒ እንደተናገሩት በዚህ አሰራር መሰረት በተያዘው የምርት ዘመን በአማራ፣ኦሮሚያ፣ትግራይና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 228 ወረዳዎች ከ400 ሺህ በላይ ኩንታል ዘር ተሰራጭቷል።

ስንዴ፣ገብስ፣በቆሎ፣ጤፍ እና ሰሊጥን ጨምሮ ስምንት የእህል ዘሮችን ነው በዚህ የግብይት ስርዓት ለአርሶ አደሮቹ መሰራጨቱ ተገልጿል።

በግብይት ስርዓቱ በአምራቾቹ ውድድር በመኖሩ አርሶ አደሩ በጥራትም ሆነ በዋጋ የተሻለ ምርት በወቅቱ እንዲያገኝ አስችሎታል ብለዋል።

አምራቾች በቀጥታ ከገበሬዎች ጋር በመገናኘታቸው ክልሎች ለዘር መሰብሰቢያ ሊያውሉት የነበረው 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለሌላ ልማት እንዲሆን አግዟል ብለዋል።

ግብይቱ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በመደበኛ ስርጭት ከ30 እስከ 40 በመቶ ዘር አድሮ ለቀጣይ የምርት ዘመን ይተላለፍ የነበረውን የዘር መጠን በዚህ ሰርዓት ከ10 በመቶ በታች ማድረስ መቻሉንም ገልፀዋል።

የግብርናና እንስሳት ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እያሱ አብርሃ በበኩላቸው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ግብዓት ለማምረት ዘርን በብዛት ለመጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ 72 በመቶው ዘር በመንግስት ሲባዛ ቀሪው በግል ባለሀብት፣በህብረት ስራ ማህበራትና በዘር አምራች ማህበራት እንደሚባዛ ጠቁመዋል።

ወደፊት የህብረት ስራ ማህበራትንና የግል አምራቾችን በማብዛት ምርታማነትን ማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የቀጥታ ዘር ግብይት ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ከልል ግብርና ቢሮ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሁለት ወረዳዎች በ2002 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን አሰራሩ ውጤት በማስገኘቱ ወደ ሌሎች ክልሎች ተስፋፍቶ እየተተገበረ ነው።

አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2010(ኢዜአ)