ዜና ዜና

ኩባንያዎቹ ብረት የማምረት አቅማቸውን ወደ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ ተስማምተዋል

በብረት ማዕድን ቁፋሮ የተሰማሩ ሁለት ኩባንያዎች የዓመት የማምረት አቅማቸውን ከ155 ወደ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ መስማማታቸውን የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ገለጸ።

ይህም አገሪቱ የገቢ ምርትን በመተካት በዓመት ለዚሁ ታወጣ የነበረውን 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መቀነስ ያስችላታል ብሏል።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቴድሮስ ገብረ እግዚአብሔር እንደገለጹት ዝርዝር የአዋጭነት ጥናት ካጠናቀቁ አራት ኩባንያዎች መካከል የማምረት ፈቃድ የወሰዱት ዩ.ኤስ.ኤ.ፒ እና ሰቆጣ ማይኒንግ የተሰኙ ኩባንያዎች ናቸው።

በኦሮሚያ ቢቂላል እና በአማራ ሰቆጣ አካባቢዎች ባላቸው የብረት ማዕድን ክምችትና የአዋጪነት ደረጃ በቅድሚያ ወደ ምርት ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩ.ኤስ.ኤ.ፒ የተባለው የውጭ ኩባንያ በቢቂላል አካባቢ በዓመት 120 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብረት ለማምረት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ክምችቱና የአዋጪነት ደረጃው ታይቶ ወደ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን በማሳደግ ስምምነቱ እንዲሻሻል ተደርጓል።

ለዚህ ፕሮጀክት 150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግበትም ገልፀዋል አቶ ቴድሮስ።
በተመሳሳይ ሰቆጣ ማይኒንግ ኩባንያ ቀደም ሲል በዓመት 35 ሺህ ሜትሪክ ቶን እንዲያመርት ታቅዶ የነበር ሲሆን አሁን ምርቱን ወደ 100 ሺህ ሜትሪክ ቶን እንዲያሳድግ ተደርጓል።

በዚሁ መሰረት የምርት ፍቃድ ውል መፈፀሙንና ፕሮጀክቱም 200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሆንበት ጠቁመዋል።
የኩባንያዎቹ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መሟላታቸውንና በገቡት ውል መሰረትም የፕሮጀክት ግንባታቸውን በማጠናቀቅ በ2011 ዓ.ም አጋማሽ ወደ ምርት ተግባር እንደሚገቡ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብረት ማምረት ስትጀምር ከውጭ አገር ብረት ለማስገባት ይወጣ የበረውን 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ማዳን ይቻላል።
ይህም የአገሪቱን የመሰረተ ልማቶች ግንባታና የኢንዱስትሪ ልማት በጥራት፣ በፍጥነትና በተሻለ ዋጋ መደገፍ ያስችላል።
የዘርፉን የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያፋጥንና ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

በመሆኑም ኩባንያዎቹ በገቡት ውል መሰረት ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ በመንግሥት በኩል የመሰረተ ልማትና የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ስራ ይጠበቃል ብለዋል።
የመሬት ካሳ ክፍያን የማጠናቀቅና ሌሎች ጉዳዮችን ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች ድጋፍና ክትትል በማድረግ የምርት ሽግግሩን ማፋጠን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአገሪቱ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በሃረሪ፣ በሶማሌና በጋምቤላ ክልሎች 28 የብረት ማዕድን መገኛ ስፍራዎች በጥናት ተለይተዋል።
ሚኒስቴሩ በተለዩት አካባቢዎች ዝርዝር የአዋጪነት ጥናት በማካሄድ ላይ ለሚገኙ ስምንት ኩባንያዎችም ፍቃድ ሰጥቷል።

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2010 (ኢዜአ)