ዜና ዜና

የመለስን አስተምሮ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ ከ400 በላይ ጽሁፎች መሰብሰባቸው ተገለጸ

የመለስን አስተምሮ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ ከ400 በላይ ጽሁፎች ተሳባስበው ለሕትመት እየተሰናዱ ነው ተባለ።

ከነዚህ ጽሁፎች መካከል በአምስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ መጽሃፎች ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ ስርዓት ላይ እንደሚመረቁም ተገልጿል።

የኢፌዴሪ ታላቁ መሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ሥነ ስርዓትን በማስመልከት የመለስ ፋውንዴሽን ዛሬ መግለጫ ስጥቷል።

የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ አቶ መለስ በሕይወት እያሉ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የጻፏቸው ከ400 በላይ ጽሁፎች ተሰብስበዋል።

የታላቁ መሪ መለስ ስራዎች በቋሚ ቅርስነት ለትውልድ እንዲተላለፉ የተሰሩ ስራዎች አነስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ፤ "እስከ አሁን በተደረገው ጥረት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ ጽሁፎች ተሰባስበዋል" ብለዋል።

ከነዚህም መካከል በገጠር ልማት፣ በኢንዱስትሪ ልማት እና በውጭ ጉዳይና ደህንነት ዙሪያ ያተኮሩ መጽሃፎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአቅም ግንባታ ዙሪያና 'የዴሞክራሲ ጥያቄ በኢትዮጵያ' በሚል ርዕስ የተጻፉ አምስት መጽሃፎች "ከነገ ጀምሮ በሚደረጉ የመታሰቢያ ሥነ ስርዓት ላይ ለምረቃ ይበቃሉ" ብለዋል።
የዘንድሮው የመታሰቢያ ሥነ ስርዓትም በችግኝ ተከላ፣ በስፖርታዊና በኪነ ጥበባዊ ክንውኖች እንዲሁም በመለስ አስተምሮ ዙሪያ በተለያዩ የአገር ውስጥና በውጭ ምሁራን የሚቀርብ ጽሁፎችና የፓናል ውይይቶችም እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ጽሁፎቹም በልማትና በልማታዊ አስተሳሰብ፣ በፌዴራልዚም፣ በሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ብዘሃነት ላይ ያተኮሩ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።
ለሁለት አስርት ዓመታት በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚነስትርነት የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ የተሰውበት አምስተኛ ሙት ዓመት "የሀሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

አዲስ አበባ ነሃሴ 5/2009(ኢዜአ)