ዜና ዜና

ዘንድሮ በመስኖ ከለማው መሬት 370 ሚሊዮን ኩንታል ይጠበቃል-የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር

በያዝነው አመት በአገሪቱ በመስኖ ከለማው መሬት 370 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ መልማቱም ተገልጿል፡፡

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ በተለይም ድርቅ የሚያጠቃቸው ቆላማ ክልሎች ያላቸውን ሰፊ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ የመስኖ ልማቱ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን የህዝብ ግንኙነቱ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋምና ተፈላጊ ምርቶችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ረገድ የመስኖ ልማቱ ስራ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የመስኖ ልማቱን ስራ ለማስፋፋትና አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በዚህም ረገድ አርሶና አርብቶ አደሩ የሚሰጠውን ምክርና ድጋፍ ተግባራዊ በማድረግ የጎርፍ ውሃን በማቆርና አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ድርቅ መከላከል እንደሚገባ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ኢቢሲ፣ሚያዝያ 10፣ 2009