ዜና ዜና

ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች የሰብል ምርት ወደ 316 ሚሊየን ኩንታል አድጓል - የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር

ከግንቦት 20 ድል በኋላ በተከናወኑ ስራዎች የሰብል ምርት ከ62 ሚሊየን ወደ 316 ሚሊየን ኩንታል ማደጉን የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት ግብርና ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከ36 በመቶ በላይ ድርሻ ሲኖረው፥ ኢኮኖሚው በተከታታይ እድገት ሲያስመዘግብም ግብርናው ትልቁን ድርሻ ይዞ ቆይቷል። 

በቅርቡ የአገልግሎት ዘርፉ ድርሻ የበላይነት እስከያዘበት ጊዜ ድረስ የግብርናው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ቀዳሚ ነበር።

በዚህም በመስኖ ልማት እና በክላስተር ወይም ኩታ ገጠም እርሻ የበርካታ አርሶ አደሮች ህይወት ተቀይሯል።

ለተመዘገበው እድገትም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ መውጣቱና የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩ በምክንያትነት ይነሳል።

የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ኢያሱ አብርሃ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ግንቦት 20 በግብርናው ዘርፍ ለውጥ እንዲታይ አድርጓል ብለዋል።

የሰብል ምርት ወደ 316 ሚሊየን ኩንታል አድጓል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች ቁጥርም ከ43 በመቶ ወደ 23 በመቶ መውረዱንም ተናግረዋል።

በግብዓት አጠቃቀምም አርሶ አደሩ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰው፥ ባለፉት አመታት በተሰራ ስራ የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ተጠቃሚነት እያደገ 10 ሚሊየን ኩንታል ደርሷልም ነው ያሉት፤ የምርጥ ዘር አጠቃቀሙም እድገት ማሳየቱን በመጥቀስ።

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አርሶ አደሩ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ እና ከዚህም የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ሲሰራ መቆየቱንም ያነሳሉ።

ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣ ገባነት ቢታይም የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት በኩልም የግብርናው ዘርፍ እድገት እየታየበት መሆኑም ይነገራል።

ቡና፣ የቅባት እህልና የጥራጥሬ ሰብሎችም ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙት የግብርና ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በበጀት አመቱ ስምንት ወራት ውስጥም ሀገሪቱ ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 478 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም፥ 144 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ ደግሞ 492 ሚሊየን ዶላር አግኝታለች።

የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴርም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ብሎም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ግንቦት 17 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)