ዜና ዜና

በጋሞጎፋ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 301 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ የተፈጠረው የህዝብ መነቃቃት በልማቱም መደገም እንዳለበት የደቡብ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ አሳሰቡ፡፡

በጋምጎፋ ዞን 15 ወረዳዎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ለአንድ ወር ያህል ሲዘዋወር የቆየው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ማጠቃለያ ፕሮግራም ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል ፤ 301 ሚሊዮን ብርም ተሰብስቧል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት የዞኑ ህዝብ የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የሰጡትን አደራ ጠብቆ በመደገፍ ያሳየውን አንድነትና የነቃ ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡

"ዞኑ በግብርና ፣ በቱሪዝምና በሌሎች የልማት መስኮች እምቅ ሃብት ያለው በመሆኑ የተፈጠረዉን የህዝብ መነቃቃት ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል"፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ ዋንጫው በዞኑ በሚኖረው ቆይታ 270 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ ወደ 301 ሚሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል ፡፡

ባለሃብቶች ፣ የመንግስት ሠራተኞች ፣ ነጋዴዎች ፣ አርሶ አደሮች፣መንግሰታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎችም ነዋሪዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን የደቡብ ምዕራብ ቀጠና አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ጦና በሰጡት አስተያየት ተቋማቸው ለግድቡ ግንባታ 1 ሚሊዮን 20 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ እንዲውል የሚገዙት ቦንድ የቁጠባ ባህላቸውን ለማሳደግ እንደረዳቸው የተናገሩት ደግሞ በዞኑ የኦይዳ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አታርቄ አሎ ናቸዉ ፡፡

በግላቸው የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንና ድጋፋቸውን ወደፊትም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 10/2009 /ኢዜአ/