ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም

በውስጣዊ ጥንካሬያችን፣ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶቻችንን እናስቀጥል!
በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው፣ አገራችን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ሊኖራት የሚችለው በቅድሚያ ውስጣዊ ጥንካሬን መፍጠርና በሂደትም እያዳበረች መሄድ ስትችል ነው።
በዚሁ መሠረት፣ ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በማጎልበት ረገድ በቅድሚያ በውስጣችን የቅራኔ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ፣ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ መንግሥት እና ህዝብ በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ላለፉት ዓመታት ለአገራችን ህልውና፣ እድገትና ብልጽግና መሠረታዊ ጉዳይ የሆነው ሰላም በአስተማማኝ መልኩ ሰፍኖ ቆይቷል። አሁን ላይ እዚህም እዚያም የሚታዩ ጊዜያዊ ያለመረጋጋት ችግሮች ቢኖሩም፣ በምንኖርበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገራት ጋር በተነፃፃሪ ሲታይ አሁንም ድረስ ሰላሟን ያረጋገጠች አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት።

በአገራችን ረዘም ላለ ጊዜ፣ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑ ደግሞ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንድናተኩር ያስቻለን ሲሆን ሁሉን አቀፍ የሆነ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማምጣት በዓለም ላይ ፈጣን እና ተከታታይ እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ በጣም ጥቂት አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት እንድንሰለፍ አስችሎናል።

አገራችን ኢትዮጵያ ከዬት ተነስታ የት እንደምትደርስ ራዕይ አንግባ፣ ሕዝቦቿም ጥንታዊ ሥልጣኔዋን ለመመለስ በቁጭት ተነሳስተው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እየገነቡ ያሉባት፣ በዚሁ ሂደት ውስጥም የአፍሪካ አገራትን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች ያለች ነች።

እያደረገችው ላለው ጥረት እና በጥረቷም ላስገኘቻቸው ድሎች እውቅና እና ምስክርነት ከሰጣት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ዛሬ እየገነባችው ያለው ግንኙነት የጥንቱን ታሪኳን በመተረክ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ እየሰራው ባለው ተጨባጭ ገድል ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም በመሆኑ፣ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በበለጸጉ አገራት የምትፈለገው እንደቀድሞው ዘመን በእርዳታ ሰጪነትና ተቀባይነት ስሜት ሳይሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በአጋርነት ለመፈጸም ነው። የምሥራቁም ይሁን የምዕራቡ፣ የበለፀገውም ይሁን በማደግ ላይ ያለው ህዝብ ሁሉ ዓይን የሚያርፍባት ተፈላጊ አገር ሆናለች።

በተለይም፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ልዕለ ኃይላኑን ጨምሮ የበለፀጉ አገራት ዛሬ የሚፈልጉን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በዋነኝነት በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ለመመካከርና ለመወሰን መሆኑ ዛሬ አገራችን የደረሰችበትን ከፍታ የሚያመላክት ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን በመሳሰሉ ተግባራት ለህዝቦች ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ዋነኛ ተዋናይ እስከመሆን ልትደርስ የቻለችው በቅድሚያ የራሷን ሰላም ለማረጋገጥ እና በተገኘው ሰላም አማካኝነትም ለእድገትና ብልጽግና አተኩራ በመስራቷ ነው።

በሁለትዮሽ ግንኙነትም ቢሆን ከበርካታ የበለፀጉ አገራት ኢንቨስትመንትን በመሳብ በዓለም የመሪነቱን ቦታ ከያዙት አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት መጠቀስ ችላለች።
በአጠቃላይ፣ ከላይ የተጠቀሱትና የመሳሰሉት የዲፕሎማሲ ስኬቶች የመጡት ውስጣዊ ሰላማችንን እና ልማታችንን በማረጋገጥ ረገድ ላለፉት ዓመታት በሰራነው ስራ ነው። ይህንኑ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው።
በመሆኑም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠመንን ያለመረጋጋት ችግር ትውልዱ በፍጥነት ሊያስቆመው የሚገባ ነው። ማንኛውም ችግር ሊፈታ የሚችለው በሰለጠነ አካሄድ፣ በመወያየትና በመመካከር እንጂ በሁከትና ብጥብጥ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።

ዱሮ፣ በኋላቀርነትና በተረጂነት ሲያውቀን በነበረው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ፣ ዛሬ እውቅናና ከበሬታ ያገኘነው ውስጣችንን ሰላም አድርገን በልማታችን ላይ በማተኮራችን፣ በየጊዜው ሲያጋጥሙን የነበሩትን ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ህጋዊ መንገድ እየፈታን በመምጣታችን መሆኑን በመገንዘብ፣ መላው ሕዝባችን የየአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና በማስጠበቅ ረገድ የሚጫወተውን የመሪነት ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌዴሪ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

ውስጣዊ ጥንካሬያችን የፈጠረልንን ድሎች ለማስቀጠል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታትና ህዝባችን ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ በመንግስት የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ከዳር ለማድረስ እያንዳንዱ ዜጋ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ጥሪውን ያስተላልፋል።