ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ-ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም

የድህነት ተራራ የሚናደው በዕውቀት ጥይት ነው!
ዘንድሮ በጠቅላላው ከ150 ሺህ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የሚመረቁ ምሁራን ብዛት ከ125 ሺህ በላይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መንግስት ለሁሉም ተመራቂዎችና ለቤተሰቦቻቸው እንኳን ደስ አላችሁ እያለ ለተመራቂዎች መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላችሁ ምኞቱን ይገልጻል።

ታላቁ መሪ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት የድህነት ተራራ የሚናደው በዕውቀት ጥይት ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የትምህርት ዘርፉ ከመንግሥት ጠቅላላ ዓመታዊ በጀት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ በማድረግ ትምህርት በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ በውጤቱም ዛሬ ከ28 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በትምህርት ገበታ ላይ ለማሳተፍ ተችሏል።

መንግሥት ቀደም ባሉት ዓመታት ካስገነባቸው 36 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪ በሚቀጥለው ዓመት ሌሎች 11 ዩኒቨርስቲዎችን ወደሥራ በማስገባት አዳዲስ ተማሪዎችን እየተቀበሉ እንዲያስተምሩ ይደረጋል፡፡ ይህን ያህል ተቋማትን በማደራጀት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን እያስተማሩ በየዓመቱ ማስመረቅ ምን ያህል ሃብት እንደሚጠይቅ መገመት አያዳግትም። በተጨማሪም መንግስት የግል ባለሃብቱን በማበረታታት በርካታ የግል ተቋማትም ተፈጥረው ተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ በየዓመቱ በከፍተኛ ትምህርት እየሰለጠነ ወደሥራ የሚገባው የሰው ሃይል ብዛት እየጨመረ የመጣ ሲሆን ይኸው ሂደት በቀጣይ ዓመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

በአገራችን ለዘመናት የቆየውን ድህነት በማስወገድና በሂደትም ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በማሸጋገር በኢኮኖሚያችን ላይ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በዕውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአመለካከቱ እና በአምራችነት ስነምግባሩ የታነፀ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። ይህንኑ በመገንዘብም መንግሥት በአንድ በኩል አጠቃላይ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ዕድገቱ የሚጠይቃቸው የኢንጂነሪንግና የሂሳብ ትምህርቶች እንዲስፋፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። ትምህርትን ከማስፋፋት ባሻገርም ጥራቱን ለማሻሻል የጥራት ፓኬጆችን አዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ ሲረባረብ ቆይቷል። ከዚሁ ጎን ለጎን በጥራቱና በቁጥር እያደገ የመጣውን የሰው ሃይል በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባትም ልዩ ልዩ ፓኬጆችን አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ጥረቱ ፍሬ እያፈራና በርካታ ወጣቶችን ሥራ ፈጣሪዎች እያደረገ ነው። በተጨማሪም 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ወጣቶች የቢዝነስ አስተሳሰብ ይዘው በቀጥታ ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገቡ ለማስቻል ጥረቱ ቀጥሏል።

ውድ ተመራቂዎች! ይህቺ አገር ካላት አነስተኛ ጥሪት ላይ መድባ ያስተማረቻችሁ ወድ ልጆቿ ናችሁ፡፡ አገራችን ከድህነት እና ኋላቀርነት ለመላቀቅ እና ብሎም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ትችል ዘንድ ተቀጥሮ ከመስራት በላይ ራዕይ እንዲኖራችሁ ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም ሥራን ከመጠበቅ ይልቅ በየተማራችሁበት የትምህርት መስክ በመደራጀት መንግሥት በነደፋቸው ፓኬጆች ተጠቃሚ እንድትሆኑ መንግስት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

ውድ የተመራቂ ቤተሰቦች! አስተምራችሁ ለማስመረቅ በመብቃታችሁ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ። ምረቃው በተመራቂዎች ህይወት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያለው ነው። በማስከተልም ለቀጣዩ ህይወታቸው ትኩረት በመስጠት ሥራን ሳይንቁና ሳይመርጡ እንዲሰሩ ስነልቡናቸውን በማዘጋጀት፣ ተነሳሽነታቸውን በማጎልበት፣ ቁጠባን በማበረታታት እንዲሁም አስፈላጊውን ሞራል እና አቅም ከፈቀደም ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት ለሥራ ፈጣሪነት እንድታበረታቷቸው መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

ተመራቂዎችን በአስፈላጊው ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት ቀርጾ በማውጣት ረገድ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወታችሁ ላላችሁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ አስተዳደሮች እና መምህራን! የድህነት ተራራ ማፍረሻ ጥይቶችን በማቀበል ረገድ ለአገራችን እያደረጋችሁት ላለው ጉልህ አስተዋጽዖ መንግሥት ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ በአጠቃላይ አገራችንን ከድህነት ማላቀቅ እና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ እንድንችል ዜጎች ሁሉ የሥራ ክቡርነትን ተቀብለን በየተሰማራንበት መስክ ሁሉ ውጤታማ ሆነን እንድንገኝ የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።