ዜና ዜና

በሰሜን ወሎ 3ሺህ 600 የአይን ሞራ ግርዶሽና የትራኮማ ህሙማን በቀዶ ህክምና ማየት ችለዋል- የዞኑ ጤና መምሪያ

በሰሜን ወሎ ዞን በአይን ሞራ ግርዶሽና ትራኮማ የተጠቁ 3ሺህ 600 ህሙማን በተደረገላቸው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማየት መቻላቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

 የመምሪያው የዓይነ ስውርነት መከላከል ባለሙያ አቶ አስፋው ጎበዜ እንደገለጹት ህሙማኑ ብርሃናቸው የተመለሰው ባለፉት ሰባት ወራት በወልድያ፣ በቆቦ፣ በላልይበላ ሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች በመደበኛና በዘመቻ መርሀግብር በተደተገላቸው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ነው።

 በበሽታዎቹ የሚያዙ ሰዎች በግንዛቤ እጥረት ወደ ህክምና ተቋም በወቅቱ መምጣት ባለመቻለቸው ህክምናውን አስቸጋሪ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል ።

 በወልድያ ሆስፒታል የዓይን ቀዶ ህክምና ባለሙያ አቶ አብርሃም አረጋዊ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ከተደረገላቸው 1ሺህ 750 ህሙማን በተጨማሪ ለ3ሺህ 250 ህሙማን የተለያየ የአይን ህክምና ተሰጥቷል ።

 የግልና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ በተለይ ለትራኮማ ክትባት መውሰድና ቫይታሚን ኤ ያሉባቸውን ምግቦች መመገብ የአይን ህመሞችን አስቀድሞ ለመከላከል መፍትሄ መሆናቸውን መክረዋል ።

 በመቄት ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሰጠችኝ አያሌው በሰጡት አስተያየት በዚህ አመት በወልድያ ሆስፒታል ለሁለት አይናቸው ሁለት ጊዜ በተደረገላቸው የቀዶ ህክምና የአይናቸው ብርሀን መመለሱን ተናግረዋል ።

 ከራያ ቆቦ ወረዳ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ወይዘሮ ዘነቡ ካሳው በበኩላቸው "በተደረገልኝ የቀዶ ህክምና በሞራ ግርዶሽ ለሁለት አመት ማየት ተስኟቸው የቆዩ ሁለት አይኖቼ ማየት ችለዋል " ብለዋል ።

 "ከዓይን ቆቤ በሚበቅል ፀጉር ከሚያስከትልብኝ ሲቃይ ለመገላገል በየጊዜው በወረንጦ እየነቀልኩ ለ40 አመት ቆይቻለሁ " ያሉት አቶ ፈንታየ ገብሬ በበኩላቸው በህክምና ከበሽታው መዳን እንደሚቻል በማወቃቸው በሆስፒታሉ የአይን ቆብ ህክምና ለማድረግ ወረፋ እየጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

ወልዲያ መጋቢት 3/2010 /ኢዜአ