ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ጷጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም

በአዲሱ ዓመት ለተሻለ ሃገራዊ ውጤት በጋራ እንዘጋጅ!
መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንኳን ለመጪው አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ፣ ዓመቱ የሰላም፣ የጤና፣ የልማትና የብልጽግና እንዲሆንላችሁም የመ/ኮ/ጉ/ ጽ/ቤት ከወዲሁ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ፣ በተለይም በአንደኛው ሚሌኒየም ወቅት ከፍተኛ የሥልጣኔ ማማ ላይ ደርሳ እንደነበር፣ በሁለተኛው ሚሌኒየም የመጀመሪያዎቹ 300 ዓመታትም ውስጥ እንደዚሁ በስልጣኔ ማማ ላይ መቆየት ችላ እንደነበር ይታወቃል። ለዚህም ለዓለም ያበረከተቻቸው በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች እስካሁን ህያው ሆነው እየመሰከሩላት ይገኛሉ። በረጂሙ ታሪኳ ውስጥ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች፣ ይልቁንም ለዓለም ጭቁን ህዝቦች ሁሉ የነጻነት ቀንዲል ተደርጋ የምትወሰድ አገር መሆኗም በመላው ዓለም በገሃድ ይታወቃል።

ይሁንና ያንን የቀድሞ ስልጣኔያችንን በሁለተኛው ሚሌኒየም የመጨረሻ ክፍለ ዘመናት ወቅት ማስቀጠል ሳንችል ቀርተናል። እንዲያውም ከስልጣኔያችን ቁልቁል ወርደን የዓለም ጭራ፣ የአስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት፣ እንዲሁም የእርስ በርስ ጦርነት ተምሳሌት እስከመሆን ደርሰን ነበር። ውድቀታችንን ያፋጠነው መሰረታዊ ጉዳይ የቀድሞ አምባገነን አገዛዞች አብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻላቸው የተነሳ በአገራችን ለረጂም ጊዜ የቆየው የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ እጦት ያስከተሏቸው መዘዞች ነበሩ።

ዛሬ ያለፈውን አስከፊ ታሪክ ከመሰረቱ መቀየር የቻልንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በዚህም አገራችን በአንጻራዊነት ሲታይ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነቷን ማስጠበቅ የቻለች፣ ፈጣንና ተከታታይ እድገት ማስመዝገብ የቻለችና በስኬቶቿም የብዙ አገራትን ቀልብ እየሳበች የመጣች አገር መሆን ችላለች።

በተለይም የዛሬ 10 ዓመት ሦስተኛውን ሚሌኒየም በተቀበልንበት ወቅት አገራችንን ወደቀድሞ ታላቅነቷ ለመመለስ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድ ድምጽ የገባነውን ቃል ጠብቀን ባለፉት 10 ዓመታት በድህነት ላይ ባካሄድነው መጠነ ሰፊ ትግል ያስመዘገብነው አንጸባራቂ ድል በእርግጥም ለመጪው ትውልድ ልማትን እንጅ ልመናን እንደማናወርስ ማረጋገጫ ሆኖልናል። በነዚሁ አጭር ዓመታት የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችም ቀጣይ ዕድገታችንን በተሻለ ለማፋጠን እንችል ዘንድ ጥሩ መደላድል ፈጥረውልናል። በመሆኑም መጪው ዘመን የአገራችን ከፍታ ነው በሚል መሪ ቃል የ2010 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ለመቀበል ስንዘጋጅ በባዶ ተስፋ ተሞልተን እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል።

መጪው ዘመን በእርግጥም የኢትዮጵያ ከፍታ እንደሚሆን በሙሉ ልብ መተማማን የምንችለው ግን ወደ ከፍታ የሚያዳርሱንን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአዲሱም ዓመት አጠናክረን በመቀጠል አንድ እርምጃ ፈቀቅ ማለት ስንችል ነው። ይህም ማለት እያንዳንዳችን የሚጠበቅብንን የቤት ሥራ በአግባቡ ማከናወን ይጠይቀናል። ከመንግሥት ቁርጠኝነት ባሻገር ህዝባችን በልማቱ ውስጥ ሲያያደርገው የነበረውን የላቀ ተሳትፎ ማሳደግና ከልማቱም እያገኘ የመጣውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አጠናክሮ መቀጠልን ይጠይቃል።

ከዚህ አንጻር መንግሥታችን ባለፉት 10 ዓመታት በሰላም፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንዲሁም በዲፕሎማሲ መስኮች ያስመዘገባቸውን ውጤቶች በአዲሱ ዓመት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ ይወዳል። በሌላ በኩል ህዝቦቻችን በድህነት ላይ የለኮሱትን የጋራ ትግል በአዲሱ ዓመት አጠናክረው እንዲቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ማቅረብ ይወዳል።

ወጣቱ ትውልድ አገራችንን ወደቀድሞ ታላቅነቷ ለመመለስ እንችል ዘንድ በተሰማራበት የሙያ መስክ ሁሉ በአዲሱ ዓመት ጠንክሮ በመስራት፣ ዴሞክራስያዊ አስተሳሰብን ይበልጥ በመላበስና በማዳበር፣ ራስን ከተለያዩ ማህበራዊ ግድፈቶች ነፃ በማውጣት እንዲሁም ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ለተሻለ ውጤታማነት እንዲዘጋጅ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል። በዚሀ ዘመን አገርን መውደድ እና አገር ማፍቀር የሚገለጸው በዚህ መልኩ ነውና!