ዜና ዜና

ምርት ገበያው በየካቲት ወር 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር አገበያየ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በየካቲት ወር 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በወሩ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 65 ሺህ ቶን ምርቶችን ማገበያየቱን ነው አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ 29 ሺህ 415 ቶን ቡና በ2 ቢሊየን ብር፣ 28 ሺህ 929 ቶን ሰሊጥ በ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣ 5 ሺህ 660 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ88 ሚሊየን ብር እና 1 ሺህ 627 አረንጓዴ ማሾ በ30 ሚሊየን ብር ማገበያየቱንም ገልጿል።

በወሩ ለግብይት ከቀረቡ ምርቶች ውስጥ ቡና ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዝ፥ በመጠን 45 በመቶ በዋጋ ደግሞ 63 በመቶውን ድርሻ ይዟል።

ሰሊጥ ደግሞ በግብይት መጠን 44 በመቶ በዋጋ ደግሞ 33 በመቶ ድርሻን ይዟል፤ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻርም በመጠን በ2 በመቶ እንዲሁም በዋጋ ደግሞ የ45 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያለው።

ለውጭ ገበያ የቀረበ ቡና በመጠን 59 በመቶ በዋጋ ደግሞ 53 በመቶ ድርሻ ይዟል፤ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ቡና ውስጥም 15 ሺህ 789 ቶን ያልታጠበ ቡና በ983 ሚሊየን ብር መገበያየቱን ገልጿል።

1 ሺህ 671 የታጠበ ቡና በ128 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለሃገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ 4 ሺህ 93 ቶን ቡና ደግሞ በ231 ሚሊየን ብር መገበያየቱንም ነው ምርት ገበያው በመግለጫው ጠቅሷል።

የካቲት 29 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)