ዜና ዜና

ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።  

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ጀምበር ሐድጉ  እንደገለጹት ገንዘቡ የተሰበሰበው በዞኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በስጦታና በቦንድ ግዥ ባለፉት ሰባት ወራት ካደረጉት ድጋፍ ነው።

ሕብረተሰቡ ድጋፍ ያደረገው የግድቡ ግንበታ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የቦንድ ግዥ ሳምንትና የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ስነ ስርአት ላይ ነው።

በተለይ በቦንድ ግዥው የመንግስት ሠራተኞች፣ ሞዴል አርሶ አደሮችና ነጋዴዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

እንደ ወይዘሮ ጀምበር ገለጻ፣ በበጀት ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ ከቦንድ ሽያጭና ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀግብሮች ለማግኘት የታቀደውን 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እየተሰራ ነው።

የማይጨው ከተማ ነዋሪው አቶ አብርሃም ስዩም በሰጡት አስተያየት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን የአምስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

"ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊነታችንና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ " ብለዋል ።

በዞኑ የራያ አዘቦ ወረዳ ነዋሪው አቶ ህንደያ ባራኪም ለግድቡ ግንባታ ለሦስት ጊዜ ሙሉ የወር ደሞዛቸውን በመለገስ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የዞኑ ሕዝብ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ማይጨው ሚያዝያ 4/2009/ኢዜአ/