ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም.

በህገ  መንግሥታችን የተጎናፀፍናቸውን ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግራለን !

መላው የአገራችን ሕዝቦች፣ እንኳን ለ12ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን በማለት የኢፌዴሪ መንግሥት የላቀ ደስታውን ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት የጸደቀበት ዕለት፣ "የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን" ተብሎ መከበር ከጀመረበት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በዓሉ በእያንዳንዱ ክልል አስተናጋጅነት ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል። እነሆ የዘንድሮው በዓል ተረኛ አስተናጋጅ በሆነው የአፋር ብሄራዊ ክልልም በህገ መንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን"  በሚል መሪ ቃል በሰመራ ከተማ እጅግ በደመቀ ሁኔታ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

የዘንድሮው በዓል በአፋር ብሄራዊ ክልል መከበሩ በራሱ የሚነግረን አንድ ሃቅ አለ። እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ተብላ በመላው ዓለም እንድትታወቅ ያደረጓት የዝነኛዋ ሉሲ አጽም እና ሌሎች ተጓዳኝ የጥንታዊ ሥልጣኔ  አሻራዎች የተገኙት በዚህ ክልል  ነው። ክልሉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሚያደርገው ይህን መሰሉ ታላቅ እውነታ ይኑር እንጂ የቀድሞዎቹ ሥርዓቶች ይከተሉት በነበረው አገዛዝ ለዘመናት ከልማት ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቷል። ዛሬ ምስጋና ለህብረ-ብሄራዊው ፌዴራላዊ ሥርዓታችን፣ ያ አስከፊ ሁኔታ ከመሰረቱ ተለውጧል። የልዩ ልዩ ህዝቦች መኖሪያ የሆነችው አገራችን ዛሬ እየተከተለችው ባለው ህብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓት አማካኝነት ሁሉም ህዝቦች እኩል ባለቤት፣ እኩል ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሆኑባት አገር መሆን ችላለች።

ህብረ ብሄራዊው ፌዴራላዊ ስርዓታችን ስልጣንን በፌዴራልና በክልል መንግስታት በማከፋፈል፣ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣን እንዲቀዳጁ በማስቻሉ የብሄር ብሄረሰቦችን የማንነት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ፣ ሁሉም ህዝቦች ወደውና ፈቅደው አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማ አንግበው  ጠንካራ አገር ለመፍጠር እንዲረባረቡ ያስቻለም ነው። ለዚህም በበዓሉ ወቅት የታየውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ርክክብን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። ዋንጫውን ያስረከበው የደቡብ ክልል ለግድቡ ግንባታ ባለፈው ዓመት ባካሄደው የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰቡን ሲያስታውቅ፣ ዋንጫውን በተራው የተረከበው የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በበኩሉ የተሻለ ገቢ ለማሰባሰብ ቁርጠኝነቱን ገልጿል። በመሆኑም የህዳሴ ፕሮጀክቶቻችን የአገራችን ህዝቦች አንድ ጠንካራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንጻር እያካሄዱት ያለው ርብርብ አመላካች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባዋል።

በአጠቃላይ የምንከተለው ህብረ ብሄራዊው ፌደራላዊ ስርዓታችን አገራችንን የአስተማማኝ ሰላም ባለቤት አድርጓታል። ዓለምን ያስደመመ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብም አስችሎናል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የአገራችን ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም የዜጎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወት እየተሻሻለ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንም እየጎለበተ መሄዱን ቀጥሏል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ዘርፈ-ብዙ ድሎች ሊመዘገቡ የቻሉት  ህብረ ብሄራዊውን ፌደራላዊ ስርዓት መከተል ከጀመርን በኋላ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። አሁን ያጋጠሙንን ችግሮችም ከአሁን በፊት ሲያጋጥሙን የነበሩ ችግሮችን በፈታንበት አግባብ በህዝቦች ባለቤትነትና የጋራ ተሳትፎ በመፍታት ተጨማሪ ድሎችን ማስመዝገባችንን የምንቀጥል ይሆናል።

በመሆኑም  ዛሬ በሉሲዋ ምድር፣ የህብረ ብሄራዊነታችን ድምቀት እንዲህ አሽብርቆ እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመካከላቸው ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን የሰላም፣ የመቻቻል፣ የአንድነትና በጋራ የማደግ ብርቱ ፍላጎትና ጥረት ወደፊት ለማስቀጠል ካላቸው ጽኑ አቋም በመነጨ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል። እንዲሁም በመፈቃቀድና እጅ ለእጅ ተያይዘው የፈጠሯት አዲሲቷ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠልና ወደ ከፍታ ማማዋ ለማውጣት ያላቸውን ቁርጠኝነትም ማሳያ ነው። በመሆኑም በምንከተለው ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት አማካኝነት እያስመዘገብናቸው ያሉትን ዘርፈ-ብዙ ድሎች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በጋራ እንረባረብ። መልካም በዓል!