ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ከጎረቤት አገራት ጋር ያለን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል!
አገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን በማረጋገጥ ላይ ያነጣጠረ የውጭ ጉዳይ እና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ይኸው ፖሊሲያችን በዋነኝነት የሚያጠነጥነው ህዝቦቻችን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን በማድረግና ለዚሁ የተመቻቸ ሁኔታን በመፍጠር ላይ መሆኑም ይታወቃል።
ከዚህ አንጻር ከምስራቁም ይሁን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነታችንን በማጠናከር ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ለልማት የሚሆን ፋይናንስ ወዘተ በማፈላለግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የኢኮኖሚ ዲኘሎማሲ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንገኛለን። ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያም በሀገራችን፣ በአካባቢያችንና በአህጉራችን ብሎም በዓለማችን ዙሪያ ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋት እንዲሰፍን የተቻለንን ሁሉ በመሥራትም ላይ ነን፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአጎራባች አገራት፤ ለአካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሰላምና ልማት መጠናከርም አበክራ እየሰራች ትገኛለች። ይህም ዓለም አቀፍ አድናቆትና ክብር እንዳተረፈላት አይዘነጋም።

በተለይም በአፍሪካ አገራት መካከል ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ በመካከላቸውም ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ከምታደርገው ጥረት ባሻገር የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲያገኙና አህጉሪቱ በዓለም መድረክ ተሰሚነት እንዲኖራት እያደረገችው ያለው ጥረት በአህጉሪቱ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ተግባር ሆኗል።

በዚህ በኩል በተለይም ከአጎራባች አገራት ጋር፡ የህዝቦችን ጥቅም ባስቀደመ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርተን በሰራነው ተግባር አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ እና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን በግልጽ እንዳስቀመጠው፡ በጎረቤት ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፡ ይልቁንም ለሰላማቸውና ለልማታቸው የሚጠበቅባትን ዋጋ በመክፈል ጭምር ዕምነት የሚጥሉባት ጎረቤት ለመሆን ችላለች፡፡ የኃይል ልማት፣ የመንገድና የባቡር መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ሀገራቱንና ህዝቦቻቸውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረትም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና በተገቢው መልኩ ዕውቅና እያገኘ መጥቷል፡፡ በዚህም ከሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ከነዚህ አገራትም አልፎ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በተለይም ከሩዋንዳና ዩጋንዳ፣ ከታንዛንያና ቡሩንዲ ጋር ያለን ግንኙነት ጠንካራ ወደሚባል ደረጃ አድጓል፡፡ ከአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋርም ታሪካዊ የሚባል አዲስ ግንኙነት መፍጠር እየተቻለ ነው፡፡

ከነዚህ አገራት ጋር ያለንን በጎ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሲባልም በመሪዎች ደረጃ ኦፊሴላዊ ጉብኝቶችን የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለአብነትም ሰሞኑን የጅቡቲና የሱዳን ሀገራት ፕሬዚዳንቶች በአገራችን ያካሄዱት ጉብኝት፣ እንዲሁም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በታንዛኒያ ያካሄዱዋቸው ጉብኝቶችን መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ አገራችን ከራሷ ጥቅም ባለፈ ለአጎራባች አገራት ሰላም ዕድገትና ብልጽግና መረጋገጥ ብሎም ለአካባቢያዊና አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ጥቅም መረጋገጥ እያካሄደች ያለውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አጠናክራ የምትቀጥለው ይሆናል።