ዜና ዜና

በሰሜን ወሎ በ28 ሺህ 880 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የቅንጨ አረም ተወገደ

በሰሜን ወሎ ዞን ከበጋ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በተጓዳኝ በ28 ሺህ 880 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ቅንጨ አረም እንዲወገድ መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የአዝርዕት ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ልዑልሰገድ ለኢዜአ እንደገለፁት በተያዘው የበጋ ወቅት የተወገደው ይሄው አረም  በጉባላፍቶ፣ በሀብሩ፣ በራያ፣ በቆቦና በወልድያ ቆላማ ወረዳዎች በሚገኙ 78 ቀበሌዎች ውስጥ ነው።

አረሙ መልሶ እንዳይከሰት  በባህላዊ መንገድ ከስሩ ተነቅሎ እንዲቃጠል ተደግሯል።

በ58 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አረሙ ተከሰቶ እንደነበር ያመለከቱት ባለሙያው ቀሪውን የማሶገድ ስራ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ አረሙን በማሶገድ ተግባር ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል ።

አረሙ በመሬት ውስጥ ያለን ውሀና ንጥረ ነገር አሟጦ ስለሚጠቀም በተለይ ጤፍና ማሽላ ሰብልን በማቀጨጭ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የማጥፋት ባህሪ እንዳለው  አስረድተዋል።

የእንስሳት የግጦሽ ቦታዎችንም በመውረር የመኖ አቅርቦት እጥረት እያስከተለ ነው ተብሏል።

አረሙ በ1977 ዓ.ም፡ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ከእርዳታ ስንዴ ጋር ከውጭ የገባ፣ በጎርፍ፣ በእንስሳትና በሰው እግር ንክኪ በፍጥነት የመሰራጨት ባሕሪ እንዳለውም ተመልክቷል። 

በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ ስምንት  አርሶ አደር መንገሻ ንጉሱ በሰጡት አስተያየት አረሙ በአካባቢው እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በማስወገዱ ስራ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

" በስራው አረሙን ከእርሻ ማሳና ከግጦሽ መሬት ላይ ነቅለን በማቃጠል ተቆጣጥረነዋል " ያሉት ደግሞ በወረዳው የቀበሌ ሰባት አርሶ አደር አከለ አሰፋ ናቸው።

ወልድያ መጋቢት 1/2010/ኢዜአ