ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ- መጋቢት 28 ቀን 2010 ዓ.ም

ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ለህዳሴያችን ስኬት!

የኢትዮጵያ ህዳሴ ስኬት የሚረጋገጠው፣ አንደኛው ትውልድ በዘመኑ የጀመረውንና ያስመዘገበውን ውጤት ከቀጣዩ ትውልድ ጋር በመቀባበል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሂደቱም ከመናቆር ይልቅ መደጋገፍን፣ ከመጠላለፍ ይልቅ መተባበርን የሚጠይቅ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሰየም በአገራችን ታሪክ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እውን መሆኑን ዳግም በተግባር አረጋግጧል፡፡

ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩ በአንድ በኩል ዛሬ አገራችን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚያመላክት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ለቀጣይ ሰላማችንና ዕድገታችን ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም፣ አገራችን በተያያዘችው የህዳሴ ጉዞ ሂደት ውስጥ እመርታዊ ለውጥ ተደርጎ የሚወሰድ እና ለቀጣይ የዕድገት ጉዞም ትልቅ መሠረት የሚጥል ሲሆን፣ ለዴሞክራሲ ኃይሎች፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብሎም በአፍሪካና በዓለም አደባባይ ላይ ለሚኖረን ተሳትፎም በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር ነው፡፡

እንደሚታወቀው፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጣሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ናቸው፡፡

እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በተግባር ሊረጋገጡ የሚችሉት፣ በመንግሥት ጥረት ብቻ እንዳልሆነም ይታወቃል። ይልቁንም፣ መላው ህዝባችን በቡድንና በተናጠል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

በመሆኑም፣ መንግሥት የመሪነት እና የአስተባባሪነት ሚና ቢኖረውም የዜጎች ህይወት በመሠረቱ የሚቀየረው በዋነኝነት በዜጎች ጥረትና ልፋት መሆኑን መገንዘብ እና በዚህ በኩል ራሳችንን ለለውጥ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ፣ አዲሱ አመራር የሚጠበቅበትን የመሪነትና የአስተባባሪነት ሚና በአግባቡ እንደሚወጣ፣ ሕዝባችንን በባለቤትነት የማሳተፍ ነባር መርሆዎቻችንን ተከትሎም ከድህነት ለመላቀቅ የተያያዝነውን ራእይ ለማሳካት ጠንክሮ እንደሚሰራ ለማረጋገጥ ይወዳል።

አገራችን ኢትዮጵያን በ2017 ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የያዝነው ዕቅድ የሚሳካው በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሟላ እና ንቁ ተሳትፎ መሆኑን አጥብቆ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት፣ ትውልዱ አሁን ያስመዘገበውን ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ድል እየተንከባከበ ለቀጣይ ተደማሪ ውጤቶች ርብርብ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡