ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ
ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም

የዘላቂ ሰላማችን ዋስትናና ተጠቃሚ ባለቤት ህዝባችን ነው!
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ወራት በሥራ ላይ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ወስኗል። ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአዋጁን የ10 ወራት አፈፃጸም በመገምገም ነበር። በመሆኑም ለአዋጁ መደንገግ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች መቀልበሳቸውን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች አንዳንድ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን፣ ከሁሉ በላይ ለአዋጁ ተልዕኮ መሳካት ዓይነተኛ ሚና የተጫወተው ህዝባችን የሰላም ባለቤትነት ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ ችሏል።

አዋጁ የተደነገገበት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝብ ያነሳቸው የነበሩትን ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጽንፈኛ ኃይሎች የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ወደ ነውጥና ግርግር በመቀየር ሲያካሂዱት የነበረው አፍራሽ እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛና በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ሥራ መግታትና መቆጣጠር አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደነበር ይታወሳል። ከአዋጁ በፊት ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ለመመለስ የሚሳቀቁበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ፍጹም የተገፈፉበት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚታወቁበት የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት በጸረ ሰላም ሃይሎች ህገወጥ ድርጊት የመሸርሸር ዝንባሌ የታየበት ነበር። ሁኔታው በዚያው ቢቀጥል ኖሮ በአንዳንድ አገሮች የታየው ዕልቂት በአገራችን ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና አልነበረም።

አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይታወክ ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማትም ያለአንዳች ስጋት ስራቸውን ማከናወን ችለዋል። በሁከትና ብጥብጡ የተሳተፉ አካላት በፈጸሙት የወንጀል ክብደት ልክ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተችሏል። በርካታ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠር ተችሏል። በአመጽ ተግባር ከተሳተፉት እጅግ የሚበዙት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሱ የተደረገ ሲሆን ይህም መንግሥት ለህዝብ ያለውን ተቆርቋሪነትና ወገንተኝነት ያረጋገጠበት ሌላው ህዝባዊ ተግባር ነበር። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅትም ተጠርጣሪ ቢሆን እንኳ አንድም ዜጋችን ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ እንዲቋቋም ተደርጎ በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችል አካሄድ ከመጀመሪያው ተዘርግቶ ሥራው በግልጽነት ተከናውኗል።

አዋጁ በሥራ ላይ እያለ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎችን የማስፈጸም አቅም የሚያጠናክሩ ተከታታይ ሥራዎች መሰራታቸውም ሌላው ስኬት ነው። በተለይም የክልል የጸጥታ አካላት በሂደት የየአካባቢያቸውን የጸጥታ ሁኔታ በራሳቸው አቅም ለማስጠበቅ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ መደረጉ ዛሬ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከመደበኛ የጸጥታ ሥራችን አቅም በላይ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህንንም ጎን ለጎን ማረጋገጥ ተችሏል።

በመንግሥት የተያዘው የጥልቅ ተሃድሶ ዕቅድ ከበላይ አመራሩ ጀምሮ እስከታችኛው ህብረተሰብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲወርድና ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመለየትና በተቀመጠው አቅጣጫ ከራሱ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ መደላድል ለመፍጠር ማስቻሉም ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን አገራችን የተያያዘችው የልማትና የሰላም አቅጣጫችን እንዳይደናቀፍ ማድረግ አስችሏል። ይህ ደግሞ ያለ ህዝባችን ንቁ ተሳትፎና የባለቤትነት ሚና የተገኘ አይደለም። የአንዲት አገር ሰላም ለዘለቄታው የሚረጋገጠው በሠራዊት ቁጥር ብዛትና በአዋጅ እንዳልሆነ መንግሥታችን በጽኑ ያምናል። የሰላሙም ተጠቃሚ በዋነኛነት ራሱ ህዝቡ ነውና።

በዚህ አጋጣሚ መላው ህዝባችን፣ በየደረጃው ያሉ የመስተዳደር አካላት እና የጸጥታ ሃይሎቻችን የአገራችንን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስጠበቅ ለከፈሉት መስዋዕትነት የኢፌዴሪ መንግሥት አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል።

በአገራችን አሁን ያለው ሰላም ህዝብ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የልማት፣ የተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር አጀንዳዎቻችንን ለማስቀጠል ምቹ ዕድል የሚፈጥር ነው። በመሆኑም መንግሥት ከህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እያካሄደው ያለውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት መንግሥት ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።

መላው የአገራችን ህቦች፦ ከእንግዲህ ለአፍታም ቢሆን ሳንዘናጋ ሰላማችንን እየጠበቅን ሙሉ ትኩረታችንን ህዝባችንን በየደረጃው ተጠቃሚ በሚያደርገው ፈጣን ልማታችን ላይ በማድረግ አገራችን የተያያዘችውን የመካከለኛ ገቢ ራዕይ የማሳካት ርብርባችንን አጠናክረን እንድንቀጥል መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።