ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም

ችግሮቻችንን በጋራ በመፍታት የተጀመረውን የለውጥ፣ ህዝብን የማሳተፍና ተጠቃሚነቱን የማረጋገጥ ጉዟችንን እናፋጥን!

የኢፌዴሪ መንግስት በህዝብ የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፤ ይህንኑ ህዝባዊ አደራ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ብቃት ለመወጣት ይችል ዘንድ አቅሙን በማደስና በማጠናከር፣ ለበለጠ ውጤት ራሱን እያዘጋጀ ባለበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

በአገራችን ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የተመዘገቡ ስኬቶችንና በዚሁ ሂደት ውስጥ በተጓዳኝ ያጋጠሙ ችግሮችን ጊዜ ወስዶ በስፋትና በጥልቀት በመፈተሽ ለችግሮቹ መፈጠር ዓይነተኛው ምክንያት ምን እንደሆነና ተጠያቂነቱም የማን እንደሆነ ያለምንም ማድበስበስ በግልጽ ለይቶ አስቀምጧል። ችግሮቹን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበትንም አግባብ አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልገውን የተደራጀ አቅም ለመፍጠርም የሚቻልበትን ሁኔታም እያመቻቸ ይገኛል፡፡ ይህ ችግሩን ለመፍታት ግማሽ መንገድ ያህል የሚቆጠር ህዝባዊነት ነው።

መንግስት አገራችንን በዕድገት ጎዳና ከፍ ያደረጓትን ስኬቶቻችንን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት ለማስፋፋትና እና በተጓዳኝም እያቆጠቆጡና ስር እየሰደዱ የመጡትን ዋነኛ ድክመቶችና የድክመቶቹም መገለጫ ሆነው በቅርቡ የተከሰቱትን አደጋዎችና ስጋቶች ለማስወገድ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ሕዝባችን ከመቼውም የላቀ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በአገራችን ለተመዘገቡት ስኬቶች ሁሉ ዋነኛው ሚስጢር የሕዝባችን ተሣትፎ መሆኑን አበክሮ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት ለላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ መኖር እንቅፋት ሆነው የቆዩ ችግሮችን ሁሉ ለማስወገድ ቁርጠኛ መሆኑን ለህዝባችን ለማረጋገጥ ይወዳል።

መንግሥትና ህዝብ በተባበረ ክንድ በአገራችን ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ በትኩረት ሲረባረቡ እንደቆዩት እና በዚህም አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገቡ እንደመጡት ሁሉ ሌላኛው የህልውናችን መሰረት ለሆነው የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥተው በጋራ የሚረባረቡት እድል የሚፈጠር ይሆናል፡፡

የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከማጠናከር አኳያ ከመንግስት ባልተናነሰ መልኩ የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ የሚኖረውን ወሳኝ ሚና በመገንዘብም ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦችን እንዲሁም እንደ ህዝብ ምክር ቤቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎችና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር ህዝባዊ ተልዕኮአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ ስርአታችን መጠናከር እና ምህዳሩን የበለጠ ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ይደረጋል።

እንደሚታወቀው ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በተጓዝንበት መንገድ በመሠረታዊነት በህዝቦቻችን መካከል የቅራኔ ምንጮች እንዳይኖሩ በአስተማማኝ ሁኔታ መዝጋት በመቻላችን የራሳችንን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ከማረጋገጥ አልፈን ሌሎች በሰላም እጦት የሚሰቃዩ ህዝቦችን መታደግ የምንችል ብርቱ የሰላም ሃይል ሆነን ወጥተናል። ዓለምን ጭምር ያስገረመና በምሳሌነት እየተወሰደ ያለ ፈጣን፣ ተከታታይ እና ፍትሃዊነትን ያረጋገጠ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል፡፡ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በዲፕሎማሲና በሌሎችም በርካታ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻልነው እና የህዝቡ ህይወት ደረጃ በደረጃ እንዲሻሻል ያደረግነው በላቀ የህዝብ ተሳትፎ ውስጣዊ ጥንካሬያችንን አስተማማኝ ማድረግ በመቻላችን ነው።

እነዚህ ታላላቅ ድሎቻችን ለቀጣይ እድገታችን አስተማማኝ መሰረት የጣሉልን የመሆናቸውን ያህል ችግሮች ባጋጠሙን ጊዜም የመልካም ተስፋ ነፀብራቅ ሆነውልን ሰላማችንን እንድንጠብቅና የተሻለ ነገን ከወዲሁ እንድናይ በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ መዘንጋት የለበትም።

በአንጻሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠሙን ላሉት ቀውሶች መከሰት መሰረታዊ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከልም አንዱ እነዚሁ ድሎቻችን በሚፈለገው ፍጥነትና ልክ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እርካታ ባለማምጣታቸው እንደሆነም ይታወቃል።

ለተፈጠሩት ችግሮች ተጠያቂነቱን በግንባር ቀደምትነት የወሰደው ከፍተኛ አመራር ባለፉት ዓመታት ባስመዘገብናቸው ታላላቅ ስኬቶች ሳንኩራራ ስኬቶቹን ይበልጥ ለማስፋትና ችግሮቹንም ከሥር መሰረታቸው ለማስወገድ በቁርጠኝነት ተነስቷል። የህዝቡን ድምፅ በማዳመጥና ቅሬታዎቹን ከሥር ከሥር እየፈቱ በመሄድ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን በማስፋትና የህዝቡን ተሳትፎና የባለቤትነት መንፈስ በማጎልበት የህዝባችንን እርካታና አመኔታ ማግኘት የሚያስችሉንን አቅጣጫዎች አስቀምጧል። ወደ ከፍታ በመውጣት ላይ የምትገኘውን አገራችንን በላቀ የህዝብ አገልጋይነት የበለጠ ከፍ ለማድረግም በቁርጠኝነትና በጋራ ተነስቷል።

እነዚህን አቅጣጫዎች በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው ግን አቅማችንን አስተባብረን ስንንቀሳቀስ በመሆኑ የመፍትሄ እርምጃዎቹ ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ መላው ሕዝባችን በተደራጀ መልክ ሲያደርገው የነበረውን ገንቢ ተሳትፎ በማሳደግ ከመንግስት ጎን ቆሞ እንዲረባረብ የኢፌዴሪ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡