ዜና ዜና

በኦሮሚያ ክልል ሁለት ዞኖች ከ264 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማሩ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ከ264 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸው ተገለፀ፡፡

ከሐምሌ ወር መግቢያ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ድረስ ይካሄዳል፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያደታ ጭምደሳ እንዳስታወቁት በዞኑ17 ወረዳዎች በተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ170 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የዘንድሮው በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከኦሮሚያ ልማት ማህበር ጋር በቅንጅት የሚከናወን መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩት ወጣቶች የማጠናከርያ ትምህርት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ የአካባቢ ጽዳት እንዲሁም ለኤች አይቪ ህሙማን የቤት ለቤት ድጋፍና እንክብካቤ ጨምሮ በ14 ዋና ዋና የስራ ዓይነቶች መሳተፍ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታዬ በበኩላቸው በዞኑ 13 ወረዳዎች ከ94 ሺህ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል፡፡
ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የጤናና ሥነ-ተዋልዶ አገልግሎት፣ የኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ፣ ችግኝ ተከላና አካባቢ ጥበቃ ይገኙበታል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ተማሪ ወጣት መገርሳ ፈዬ እንደሚለው ሳይማር ያስተማረውን ህብረተሰብ ባለው እውቀት ለመርዳት በፍቼ ሪፈራል ሆስፒታል እያገለገለ ነው።

''በተለይ የኤች. አይ. ቪ ኤድስ እና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ ለህሙማን ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ሙያዊ እገዛ እያደረኩ ነው'' ብሏል።

ለታዳጊ ወጣቶች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆኑን የሚናገረው ደግሞ እጩ መምህር ተሻለ ድርብሳ ነው።
የ3ኛ ዓመት የስነ-ልቦና ተማሪ ብሌን ጉተማ በበኩሏ ፍቼ ከተማን ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ተናግራለች፡፡

ፍቼ/ነቀምቴ ሀምሌ 9/2009 (ኢዜአ)