ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ መስከረም 26 ቀን 2010 ዓ.ም.

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በጤናው ዘርፍ እያስመዘገብነው ያለውን ድል ኤች አይ ቪን በመቆጣጠር እናስቀጥል!

አገራችን ኢትዮጵያ ወደከፍታ ማማዋ በመውጣት ላይ መሆኗን ከሚያረጋግጡት አንጸባራቂ ድሎች መካከል በጤናው ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት ተጠቃሽ ነው። በዋነኛነት በመከላከል ላይ ትኩረቱን ባደረገው የጤና ፖሊሲዋ አማካኝነት የዜጎቿን ህይወት እንደቅጠል ሲያረግፉ የነበሩ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከልና ህክምና ለሚያሻቸው የጤና ጠንቆችም የጤና ተቋማትን በከፍተኛ ቁጥር በፍትሃዊነት በማስፋፋት የዜጎቿን ጤንነት በተሻለ መልኩ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ችላለች። በጤና ዘርፍ የተመዘገበው ውጤትም አገራችን በተደጋጋሚ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ምስክርነት ያተረፈችበት ገድሏ ሆኗል።

በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ሳቢያ ዜጎቻችን ወደ ህክምና ተቋማት ደጋግመው እንዳይመላለሱ፣ የመስራት አቅማቸው እንዳይዳከም፣ ላልተፈለገ ወጪ እንዳይዳረጉ በማድረግ ረገድ በርካታ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር ያስቻለ ፖሊሲ መተግበር በመቻላችን በተለይም በገጠሩ ክፍል የሚኖረው ሕዝባችን በቀላል በሽታዎች እየተጠቃ ለዘመናት ከምርታማነት ሲያርቀው የነበረው ሁኔታ በመሠረቱ በመለወጡ ሙሉ ጊዜውንና አቅሙን ለልማት እንዲያውል ማድረግ ተችሏል። በዚህ መላው ኢትዮጵያውያን ሊኮሩ ይገባል። የጤና ፖሊሲያችን ስኬታማ ሊሆን የቻለው በሕዝባችን የነቃና ያላሰለሰ ተሳትፎ እንዲሁም በጤና ባለሙያዎቻችን ብርቱ ርብርብ ነውና!

ዜጎቻችንን እንደ ቅጠል ሲያረግፉት ከነበሩት እና በጠንካራ ርብርብ ስርጭታቸውን መግታት ከቻልናቸው ወረርሽኞች መካከል ኤች አይ ቪ ኤድስ አንዱ እንደሆነ ይታወሳል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 4 በመቶ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥታችንና መላው ህዝባችን ባካሄዱት መጠነ ሰፊ ርብርብ በ2008 ዓ.ም ወደ 0 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ በመቻላችን አገራችን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በአርዓያነት ተጠቃሽ አገር ለመሆን በቅታለች። የዚህ ውጤት እንድምታ በጤናው ዘርፍ ስኬት ላይ በጉልህ የሚታይ ነው።

ዛሬስ? ይህ ስርጭት መልሶ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን በቅርቡ እየወጡ ያሉት መረጃዎች ማመላከት ጀምረዋል። ስርጭቱ በዚሁ ሂደት ከቀጠለም ተመልሶ ወደ አሳሳቢ ደረጃ መመመለሱ አይቀሬ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ መፍቀድ የለብንም። ከአንጸባራቂ ድላችን እንድናፈገፍግ የሚያደርገን ታሪክም፣ ልምድም የለንም። ጥለነው ወዳለፍነው ችግር እንድንመለስ የሚያስገድደን ነገር እንደሌለም ባለፍንበት የልማት ጥረታችን ሂደት ውስጥ እየተማርን መጥተናል። በመሆኑም ያገኘነውን ድል ጠብቀን ተደማሪ ድል የማስመዝገብ ጉዟችን በጤናው ሴክተር በተለይም ኤች አይ ቪን በመቆጣጠር ረገድ መቀጠል ይኖርበታል።

ከዚህ አንጻር መንግስት የህዝቦቹን ጤንነት የተሻለ ለማድረግ የቀረፀውን ፖሊሲ ተግባራዊነት በሁሉም መስክ ያለማቋረጥ በማስቀጠል የተጣለበትን ኃላፊነት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ እንደሚወጣ ለማረጋገጥ ይወዳል።

በተመሳሳይ የችግሩ መንስዔ የግንዛቤ እና የጥንቃቄ አናሳነት መሆኑን በመገንዘብ እያንዳንዱ ዜጋ የራሱንና የወገኑን ህይወት ለመታደግ፣ እንዲሁም የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ስለችግሩ በሚያውቀው ልክ ለማያውቀው ወገኑ በማሳወቅ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ብርቱ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል። ቀድመን ያስመዘገብነው አንፀባራቂ ድል ወደ ኋላ እንዳይመለስ ብቻ ሳይሆን ካለፈው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የምናደርገው ሩጫ የዛሬም፣ የነገም ብሎም የሁልጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል።