ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም

ካለፈው እየተማርን በአዲሱ ዓመት ለተሻለ ውጤት በአዲስ መንፈስ እንነሳ!
መላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እንኳን ለኢድ አልአድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ። በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆንላችሁ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡

የዘንድሮው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል እየተከበረ ያለው መላው ኢትዮጵያውያን መጪውን የ2010 አዲስ ዓመት በተለየ መልኩ እየተቀበሉ ባለበት ወቅት ነው።

″መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው″ በሚል መሪ ቃል ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ ጳጉሜ 5/2009 ዓ.ም ድረስ ባሉ 10 ተከታታይ ቀናት በሚከናወኑ ልዩ ልዩ አገር አቀፍ ፕሮግራሞች የ2010 አዲስ ዓመት ዋዜማ መከበር ጀምሯል። ዝግጅቶቹ የሚካሄዱት በመላው ኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወገኖቻችን ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ በመሆኑ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በበቂ ሁኔታ ማሳተፍ የሚያስችሉ በመሆናቸው በአሉን ልዩ ያደርገዋል።

የአገር አቀፉ ሁነት ዋነኛ ዓላማ ላለፉት አስር ዓመታት እንደሀገር ያለፍንበትን ጉዞ መለስ ብለን እንድንቃኝ፣ በዚህም የጎደሉንን እና ስኬቶቻችንን እንድንገነዘብና ለመጪው አዲስ ዓመት ለተሻለ ስኬት እንድንተጋ በአዲስ መንፈስ ማነሳሳት ነው።

ከሚሊኔየሙ ወዲህ ያሉትን የ10 ዓመታት ጉዞ በ10 ተከታታይ ቀናት ውስጥ እንድንቃኝና ለተሻለ ውጤት እንድንነቃቃ የቀረበውን ይህንን በተከታታይ ተግባራት የታጀበውን ልዩ ሁነት ሀሳብ ከማመንጨት እስከትግበራው ድረስ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ልዩ ልዩ አካላት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን ማቅረብ ይወዳል።

አገራችን ኢትዮጵያ ትታወቅበት ከነበረው የስልጣኔ ማማ ቁልቁል ወርዳ የስንዴ ልመና ተምሳሌት እስከመሆን ያደረሳትን የማሽቆልቆል ታሪክ ለመቀየር በቁጭት የተነሳሳው የአሁኑ ትውልድ በነዚህ ሁነቶች አማካኝነት አፈጻጸሙን መገምገሙ ተገቢና ትክክለኛ አካሄድ ነው።

እርግጥ ትውልዱ በነዚህ ዓመታት ባካሄደው ብርቱ ትግል ዛሬ በርካታ ተጨባጭ የልማት ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉ አያጠያይቅም። በዚህ ትውልዱ ሊኮራ ይገባዋል። ይሁንና ከስኬቶቻችን ጀርባ በርካታ ፈተናዎችም አጋጥመውናል። ለአብነት ያህል በመንግሥት ሥልጣን የተዛባ አተያይ ምክንያት ተንሰራፍቶ የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን መጥቀስ ይቻላል። ለህዳሴ ጉዟችን እንቅፋት የሆኑትን ተግዳሮቶች ሁሉ በጥልቅ ተሃድሶ በመለየት ችግሮቹን አንድ በአንድ ለመፍታት ያለማቋረጥ እየተካሄደ ያለው ሥራም የጉዞአችን አንድ አካል ነው።

በስኬታማ ጉዟችን ውስጥ እንቅፋት የሚፈጥሩብንን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በጽናት እየታገልን እና ህዝባችንን በማሳተፍ እየፈታን በአሸናፊነት እየተወጣን መምጣታችን አሁን ያጋጠሙንን ጊዜያዊ ችግሮች በድል አድራጊነት መወጣት እንደምንችል ያመላክታል። መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ እንደሚሆን በልበ ሙሉነት እንድንናገር የሚያደፋፍረንም በትግሉ ሂደት ያዳበርነው ችግሮችን በአግባቡ የመፍታት ምርጥ ተሞክሮ ስላለን ነው።

በዚህ መልኩ ላለፉት10 ዓመታት ያለፍንባቸውን ጉዞ መገምገማችን ለአዲሱ ዓመት የተሻለ አቅም ይፈጥርልናል። ለዚህ ደግሞ በህዝብ ባለቤትነት በየአካባቢው እየተካሄዱ ያሉት የአዲስ ዓመት መቀበያ ልዩ መርሃ ግብሮች ጥሩ መድረኮች ናቸውና ሁላችንም በንቃት እንድንሳተፍባቸው የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።

ስኬቶቻችንን የሚያጠናክሩ እና ድክመቶቻችንን በቀጣይነት በጋራ ለመፍታት የሚያስችል የተባበረ አቅም የሚፈጥሩልን ተከታታይ ሁነቶች የሚከናወኑት በውጭ አገራትም በመሆኑ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በንቃት እንድትሳተፉና ለተሻለ የህዳሴ ውጤት ራሳችሁን እንድታዘጋጁ መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

ባነገብነው ራዕይና ባስቀመጥነው ግብ ወደ ታላቅነታችን የመመለሳችን ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በመሆኑም ያለፍንበትን ጉዞ እየቃኘን፣ ከጥንካሬዎቻችንንና ከድክመቶቻችንን በመማር ለአዲሱ ዓመት ለተሻለ ውጤት ሁላችንም በጋራ እንነሳ! የኢትዮጵያችን የስኬት ከፍታ የሚረጋገጠው በማያቋርጠው የመንግስትና የህዝባችን የጋራ ጥረት ነውና።