ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም

ችግሮቻችንን በሰለጠነ አኳሃን በጋራ እየፈታን ለተሻለ አገራዊ ለውጥ እንትጋ !
ላለፉት ዓመታት ባካሄድናቸው የልማት ጥረቶች አገራችንን በሁለንተናዊ የእድገት ምህዋር ውስጥ እንድትቀዝፍ ማድረግ ችለናል። በመንገድ፣ በባቡርና በአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች፣ በቤቶች ግንባታ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ በሃይል አቅርቦት እና በመሳሰሉት ዘርፎች የጀመርናቸው የህዳሴ ፕሮጀክቶች የሃገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በመሰረቱ የመለወጥ ብሩህ ተስፋ ከመፈንጠቅ አልፈው ተጨባጭ ውጤቶችንም እያስገኙልን ናቸው።

የግጭትና የድህነት ዋነኛ መናኸሪያ በሆነው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ እየኖርን በአንጻራዊነት የራሷን ሰላም አስጠብቃ ለሌሎች አገራት የሰላም ዋስትና መሆን የቻለች፣ የኢኮኖሚ አቅሟን በጥሩ ሁኔታ እየገነባች ያለችና ውስጣዊ ጥንካሬዋ የዲፕሎማሲ ጥንካሬዋን እያጎለበተው መጥቶ ተሰሚነቷም በየጊዜው እየጨመረ የመጣች አገር ባለቤት ሆነናል።

ይህም ሆኖ ግን አሁንም ያልፈታናቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉብን ይታወቃል። የድህነት ቅነሳ አፈጻጸማችን ትልቅ ዕመርታ የተመዘገበበት የመሆኑን ያህል አሁንም 22 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው ህዝባችን ከድህነት ወለል በታች የሚገኝ ነው።

በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ወጣቶቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር የቻልን ቢሆንም አሁንም የሥራ አጥ ወጣቶቻችን ቁጥር ከፍተኛ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን በምንፈልገው ልክ አለመጓዙ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የተንሰራፋ መሆኑ፣ የወጣቶች ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ሌሎችም ችግሮች ተደራርበው የህዝባችን፣ በተለይም ደግሞ የወጣቶቻችን የብሶት ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል።

መንግሥት የእነዚህ ችግሮች መንስኤ በጥልቀት በመመርመር በአመራሩ ድክመት የመጡ መሆናቸውን በይፋ መቀበል ብቻ ሳይሆን የመፍቻ አቅጣጫዎችን አበጅቶ ወደሥራ ገብቷል። ተጨባጭ እርምጃዎችንም መውሰድ ጀምሯል።

ከነዚህም መካከል፣ በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ክሳቸው እንዲቋረጥ፣ በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ ማድረጉ ይጠቀሳል።

በፍትህ ዘርፉ የሚታየውን የዳኝነት ሂደት መጓተት ችግር ለማስቀረትም በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

በኢትዮ-ሱማሊና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታትና ከፍተኛ በጀት ጭምር በመመደብ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ተጀምረዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ይታዩ የነበሩ አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈቱም ማድረግ ተችሏል። በአጠቃላይ የተለዩት ችግሮቻችን ሁሉ በፈርጅ በፈርጅ ተለይተው በፌደራልና ክልል አመራሮች ባለቤትነት እንዲፈቱ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አገራችንን ወደኋላ የሚመልሱ አመለካከቶችና እንቅስቃሴዎች በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲከሰቱ ታይተዋል። አንዳንድ ወገኖች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንገብ በዜጎቻችን ህይወት፣ ሃብትና ንብረት ላይ እንዲሁም በመንግሥትና በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ጥቃትና ውድመት ሲፈጽሙ ታይተዋል።

ይህን መሰሉ እርምጃ፣ በአዲስ መንፈስ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ካልሆነ በስተቀር የህዝቦቻችንን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት አያስችልም! የሃገራችንን ዕድገት የማይወዱና ብሎም የተፈጥሮ ሃብቷን መጠቀም መጀመሯ ለማያስደስታቸው ኃይሎች ይጠቅም እንደሆን እንጂ ከውጪ ሆነው ወጣቱን ለአመጽና ለግጭት በመቀስቀስ በሌሎች እጅ እሳትን ለመጨበጥ ለሚሞክሩት ሃይሎችም ቢሆን የሚጠቅማቸው ነገር አይኖርም።

በከፍተኛ ወጪና በዓመታት የህዝብ ተሳትፎና ጥረት የተገነባን መሰረተ ልማት እና የግል ተቃማት እያወደሙ ተጨማሪ ልማትን ማምጣት እንደማይቻል በጊዜያዊ ስሜት ውስጥ ሆነው በአፍራሽ ተግባራት የተሳተፉ አንዳንድ ወጣቶቻችን አሁን ላይ ሆነው በሰከነ መንፈስ ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ለሃገራችን የሚበጀው፣ አሉ የምንላቸውን ማናቸውንም ህጋዊና ፍትሐዊ የዴሞክራሲ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች በሰለጠነ አካሄድ፣ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ውይይት ብቻ ለመፍታት መታገል ስንችል ነው።

በገንዘብ የማይተመነውን ሰላማችንን እየጠበቅን እና እየተንከባከብን፣ የህዝቦቻችንን ጥያቄዎች ለመመለስ፣ የወጣቶቻችንን ፍላጎቶች ለማሟላት ብሎም የተሻለ አገራዊ ስኬትን ለማምጣት የሚካሄደውን ጥረት በማገዝ ነው።

መንግሥት ብቻውን የሚያመጣው አንዳችም ነገር የለምና! በመሆኑም ችግሮቻችንን በዘለቄታው ለመፍታት እየተካሄደ ያለውን ጥረት ለማሳካት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።