ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም.

የህዝቦች የአብሮነትና የመደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ ይቀጥላል!

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ-ሶማሊ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስና በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በዘለቄታው መልሶ ለማቋቋም ልዩ ልዩ ጥረቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ይህንኑ ጥረት ለማገዝም ሰሞኑን ሦስት ክልሎች የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክተዋል፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲል የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም ከብሄራዊ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የግጭቱ አጎራባች ክልሎች የሆኑት የሃረሪ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተፈናቃዮችን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን ግጭቶቹ ተከስተውባቸው በነበሩ አንዳንድ አካባቢዎችም ተመሳሳይ የህዝብ ለህዝብ ድጋፍ ተስተውሏል።

በብሄራዊ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አማካይነት ለተፈናቃዮቹ ማቋቋሚያ እንዲውል የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ላበረከቱት የትግራይ፣ የአማራና የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ተፈናቃዮችን ተቀብሎ በማስተናገድና በተለያየ መልኩ በመደገፍ ላይ ላሉት የሃረሪ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ እንዲሁም ግጭቶች ተከስተውባቸው በነበሩ አንዳንድ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ አካባቢዎች ለታየው አኩሪ ኢትዮጵያዊ የህዝብ ለህዝብ መደጋገፍ ተግባር ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት እውቅና ይሰጣል፤ ምስጋናውንም ያቀርባል፡፡ ይኽው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ በክፉም ይሁን በደጉ ጊዜ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ናቸው። ከአብዝሃነታቸው አኳያ ያዳበሯቸው የመከባበር፣ በሰላም የመኖርና የመቻቻል፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻቸውም ዓለምን ያስደነቁ ናቸው፡፡ በታሪክ ሲወራረዱ የመጡት እነዚሁ ጠቃሚ እሴቶቻችን በአሁኑ ጊዜ በሕዝቦች መፈቃቀድ እውን በሆነችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ይበልጥ ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ይህ የሆነውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከታሪካቸው የወረሱት አብሮነታቸው አሁን ድረስ ስለዘለቀም ብቻ አይደለም። ይልቁንም የጋራ ጥቅማቸው በዘለቄታው ሊረጋገጥ የሚችለው በመፈቃቀድ አንድነታቸውን አጠናክረው ሲጓዙ መሆኑን ከልብ ተቀብለው፣ እየሄዱበት ባለው ትክክለኛና አዋጭ መንገድ መሆኑም ሊታወቅ ይገባዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ክልሎቹ ያደረጉት ድጋፍ ከቁሳዊ ጠቀሜታው በላይ የሚያሳየን ቁም ነገር አለ። ድጋፉ በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ምን ያህል የማይበጠስ ትስስርና መረዳዳት እንዳለ የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል መላ ኢትዮጵያውያን በልዩነታቸው ውስጥ የደመቀ አንድነት ፈጥረው የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው።

ድህነትን ታሪክ ለማድረግና በሂደትም አገራችን ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ ማማ ከፍ ለማድረግ እንደምንችል በእርግጠኝነት እንድንናገር የሚያደርገንም በፌዴራላዊው ስርዓታችን አማካኝነት በአዲስ መልክ እንዲቃኝ የተደረገው ይኸው የሕዝቦች ትስስር ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ህዝቦች በአካባቢዊና በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው፣ የመሪነትና የፈፃሚነት ሚና እንዲጫወቱ ያስቻለው የፌዴራል ሥርዓታችን እያስመዘገባቸው ካሉ እያንዳንዱ የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ስኬቶቻችን ጀርባ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ማሰለፍ የቻለ ነውና። የአገራዊ ስኬቶቻችን ሁሉ ምንጭ ፌዴራላዊው ስርዓታችን ነው፣ ወይም ደግሞ የፌዴራላዊው ስርዓት ባለቤትም ሆነ ጠባቂው ሕዝቡ ነው የምንለውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባዋል።

እንደስኬቶቻችን ሁሉ ችግሮች ሲያጋጥሙንም የሚፈቱት በመላው ህዝባችን ተሳትፎ እንደሆነ ያለፍንበት ሂደት አስተምሮናል። ኢትዮጵያውያን የበርካታ አንፀባራዊ ድሎች ባለቤት የሆኑት በየወቅቱ ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ በጋራ እየፈቱ በመጓዛቸው እንጂ መንገዳቸው ሁሉ የተቃና ሆኖላቸው አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። አሁን ባለንበት ወቅትም ቢሆን ያጋጠሙንን እንቅፋቶች በዘለቄታው መፍታት የምንችለው በሕዝቦቻችን የጋራ ርብርብ ብቻ ነው፡፡

በመሆኑም መላው ሕዝባችን ሰላምን በመጠበቅ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ ተፈናቃዮችን በመርዳት፣ ድርቅን በመቋቋም፣ ልማትን በማፋጠን እና በመሳሰሉት አገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተጫወተው ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።