ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ- ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም

ብሄራዊ መግባባትን ለማጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል

ብሄራዊ አንድነታችን የሰላማችን - ሰላማችንም የብሄራዊ አንድነታችን መሰረት ነው፡፡

የአገራችንን ሰላምና አንድነት፣ ብልጽግና እና ህልውና ለማስቀጠል ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገን ጠንካራ ብሄራዊ መግባባትን መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ የምንናፍቀው ደግ ነገር ሁሉ በምንናፍቀው ልክ እንደሚኖረን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ችግሮቻችንን በዘለቄታው መፍታት የምንችለውም በጠረጴዛ ዙሪያ እየተሰባሰብን ስንወያይ፣ ስንደማመጥ፣ ስንደጋገፍና ስንተጋገዝ ነው፡፡ ውይይት ንግግራችንም ከራስ ጥቅም የሚሻገር እና ከእኔ ቅድሚያ አተያይ ተላቆ የሚያይ፣ ታላቋን አገራችንን እና ታላቁን ህዝባችንን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት እያካሄደው ባለው መጠነ ሰፊ የለውጥ እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል ብሄራዊ መግባባትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን የማከናወን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳው ሆኗል፡፡

ዘንድሮ እየተከበረ ያለው የግንቦት 20 ድል በዓል መሪ ቃል "የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት" የሚለው መልዕክትም ለብሄራዊ መግባባት የተሰጠውን ትኩረት አመላካች ነው። ይሁን እንጂ ብሄራዊ አንድነታችን ከመሪ ቃልነት ተሻግሮ መሪ የህይወት መርሀችን ሊሆን የሚችለው ሁላችንም ለሰላማችን እና ለአብሮነታችን የምር ዘብ መቆም ስንችል ብቻ ነው፡፡

የአገራችንን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ አድርገን ማስቀጠል የምንችለው በቅድሚያ በእኛ ኢትዮጵያውያን መካከል መግባባት ሲፈጠር፣ ላለፈው ስህተት ይቅር ተባብለን፣ በአዲስ መንፈስ በእርቅና በፍቅር ተደምረን ስንሰራ ነው። ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር፣ መደማመጥና መግባባት መቻል አለብን፡፡

ኢትዮጵያውያን በመነጋገር፣ ሀሳብን በማክበር እና ገንቢ ምላሽም በመስጠት የረጅም ዘመን ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ በሁሉም ባህል- እምነቶቻችን ውስጥ ለሁሉን አቀፍ አንድነት እና ከስጋት ለተፋታ ሰላም የምንሰጠው ክብር እና ልእልና እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ልዩነቶቻችን መድመቂያዎቻችን እንጂ መውደቂያዎቻችን እንዳይሆኑ በጽኑ ልንረባረብ ይገባል፡፡

የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምንችለውም ከጥላቻ ሳይሆን ከፍቅር፤ ከመናናቅ ሳይሆን ከክብር፤ ከመነቃቀፍ ሳይሆን ከመደጋገፍ ወግነን በጽናት ስንቆም ብቻ ነው፡፡ የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የአመለካከት፣ ወዘተ አብዝሃነት ባለባት ውድ አገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ ቅንጦት ወይም እንደ አማራጭ የሚታይ ሳይሆን ከህልውናችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን ለዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መረባረብ የሁላችንም ተልዕኮ ሊሆን ይገባዋል፡፡ መንግስትም በኢትዮጵያችን ይህ እንዲሆን በትጋት ይሰራል፡፡

የአገራችንን ልማት ማፋጠን የምንችለውም በቅድሚያ የገናና ታሪክና የሥልጣኔ ባለቤት የነበረችው ውድ አገራችን ኢትዮጵያ፣ ዜጎቿ ከድህነት ያልተላቀቁ መሆናቸውን እና ድህነትን በፍጥነት ማስወገድ ሕልውናችንን ከማስቀጠል ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ተገንዝበን ስናበቃ የፀረ-ድህነት ትግሉን የሞት የሽረት ጉዳይ አድርገን ሁላችንም በጋራ ስንፋለመው መሆኑ ላይ መግባባት ያስፈልገናል፡፡

በአጠቃላይ፣ በቡድንም ይሁን በግለሰብ ደረጃ የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነቶች በአገራችን መኖራቸው አሁንም ይሁን ወደፊት የማይቀር ተፈጥሯዊ ዕውነታ ነው። ሆኖም ግን ልዩነቶቻችን መኖራቸው ፀጋ እንጂ ስጋት ሊሆኑ እንደማይችሉ በውል ተገንዝበን ልዩነቶቻችንን እያቻቻልን ለዚህች ታላቅ አገርና ህዝብ ትንሳኤ በጋራ መሰለፍን ከሚጠይቅ ወቅት ላይ ዘመን አገናኝቶናል፡፡

ይህን መሰሉን ብሄራዊ መግባባት ለማጠናከር እና አገራዊ አንድነትን ለመገንባት የኢፌዴሪ መንግሥት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ህዝብን ከማነጋገር ባለፈ በልዩ ልዩ መድረኮች በውጭም በውስጥም የተጠናከረ የግንኙነት ሥራ ቀጥሏል። በዚህም እጅግ ተፈላጊ የሆነው ብሄራዊ መግባባት እየጎለበተ መሄዱን የቀጠለ ሲሆን በአገራችን ላይ አንዣቦ የነበረው የስጋት ደመና ተወግዶ በምትኩ የሰላም አየር እየነፈሰ ይገኛል፡፡

እርግጥ አሁንም ቢሆን ከሰራነው ይልቅ ያልሰራነው እጅግ እንደሚበዛ መንግስት ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ለምንሰራቸው ስራዎች እና ለምንጓዛቸው የአብሮነት መንገዶች መላው ህዝባችን ከጎናችን እንዲቆምና በልዩነት ውስጥም ቢሆን ሊኖረን የሚገባውን ሀገራዊ አንድነት በጋራ እንድናጠናክር መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

መንግሥት በውጭ ከሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያቀረበው የሰላም ጥሪም ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። በኢትዮጵያውያን መካከል ቁርሾ የፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ፣ ብሄራዊ መግባባትን ለማጠናከርና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል በሽብር ወንጀል ክስ በህግ ጥላ ሥር ይገኙ እና በሌሉበትም የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸው በነበሩ ወገኖች ላይ ክስ እስከማቋረጥ የሄደበት ርቀት መንግሥት በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለብሄራዊ መግባባት መፈጠር ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ነው።

ይሄው ሂደት ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መንግሥት እያረጋገጠ በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ ሃይሎች ከሂደቱ ጠቃሚ ትምህርት ቀስመው የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ መንግሥት አሁንም የማያቋርጥ ጥሪውን ያቀርባል።

ከእንግዲህ በኢትዮጵያውያን መካከል አንዳችም ጠላትነት ሊኖር አይገባም፤ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባው ጥላቻ ሳይሆን ትብብር እና አንድነት ብቻ መሆኑን ከልብ አምኖ በመቀበል ለአገርና ለህዝብ ሲባል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል።

አሁን በተፈጠረው የለውጥ መነቃቃት እየተበረታታን፣ በትናንሽ ጉዳዮች ላይ ከመጠመድ ይልቅ ለላቀ አገራዊ ስኬት መስራታችንን እንድንቀጥል መንግስት ጥሪውን ያቀርባል። ይህንን ማድረግ ከቻልን ከታሪካዊዋ ሀገር ምድር ላይ በእርግጠኝነት ነገ ከዛሬ የተሻለ ይሆናል፡፡