ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ህዳር 22 ቀን 2010 ዓ.ም

በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ይበልጥ ይጠናከራል!

የፊታችን ሕዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን፦ በህገመንግስታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን! በሚል መሪ ቃል በአፋር ብሄራዊ ክልል በሰመራ ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡

በአገራችን ታሪክ ብዝሃነትን በማስተናገድ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጠበትን ዕለት አስመልክቶ በየዓመቱ የሚካሄደውን በዓል ሁሉም ክልሎችና መስተዳድሮች በየተራ የማስተናገድ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በዓሉ በዕኩልነት፣ በመቻቻል፣ በመከባበርና በመፈቃቀድ መርህ ላይ የተመሠረተውን ዲሞክራሲያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ የጋራ እሴቶቻችንን ይበልጥ ለማዳበርና የአገራችንና የአስተናጋጅ ክልሎችን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው። በተጨማሪም በየአስተናጋጅ ክልሎቹ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲፋጠኑ፣ ግለሰብ ባለሃብቶች በሆቴልና በሪል እሴት ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ፣ የአስተናጋጅ ክልል ከተሞች እንዲያድጉ የማድረግና የመሳሰሉ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎችንም እያስገኘልን መሆኑ ይታወቃል።

በዓሉ ህዝባችን መብቱና፤ ነፃነቱ ተከብረውለት ለፈጣን ልማትና ለአገር ግንባታ እንዲረባረብ ብሄራዊ መግባባትን እና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለይም የዘንድሮው በዓል የሚከበረው ህዝቦች ሕገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብትና ጥቅም አስከብረው የፌዴራል ሥርዓቱን የበለጠ ከማጠናከርና ከመቀጠል አኳያ የመጡበትን የተሃድሶ ጉዞ በመገምገም ለላቀ ውጤት ለመነሳሳት ቃል በመግባትና እጅ ለእጅ ተያይዘው በፍጥነት በመራመድ ነው፡፡

መንግስት ባስቀመጠው የተሃድሶ መስመር፣ በሁለንተናዊ መልኩ የታዩበትን ድክመቶች ሁሉ በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ የብሔሮችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የፌዴራላዊ ስርዓቱ የበለጠ እንዲጠልቅና እንዲደምቅ ለማድረግ ትክክለኛውን መስመር ይዞ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ በህዝቦች የነቃ ተሳትፎ፣ አንድነትና ትብብር ጉዞው እንደሚሰምርም በጽኑ ያምናል።

ከልማት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ከመፍታት ይልቅ ለግል ብልጽግና ሲባል በተጓዳኝ የሚፈፀምን የሃብት መቀራመት ችግርና የህዝቦችን አንድነት ሊሸሸረሸሩ የሚችሉ ያልተገቡ አካሄዶችን ለማረም መንግሥት በሥር ነቀል መንገድና መልሶ መላልሶ የውስጥ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛል። ተሃድሶ ሲጀመር እንደተቀመጠው የተለዩት ችግሮች በአንድ ጀምበር ታርመው የሚያልቁ አይደሉምና!

በመሆኑም ለዚህች አገርና መንግስት በጎ የማይመኙ ኃይሎች ከሚሉት በላይ ድክመቶቹን አንድ በአንድ ከህዝብ ጋር ሆኖ በሚገባ ለይቶና መውጫ መንገዶችን አበጅቶ ለመፍታት በቀጣይነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ ውጤት መመዘኛው የተሟላ የህዝብ እርካታን ማምጣት ነው፤ ከዚህ አንጻር የህዝባችንን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቀሪ ሥራዎችም በቀጣይነት እየተከናወኑ ነው። እነዚህኑ ችግሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ የህዝብ ተሳትፎና ትብብር መንግሥት እንደሚፈታቸውም ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

በተለይም አገር የመረከብን ታላቅ አደራ የተሸከመው የአገራችን ወጣት በአንድ በኩል የስራ ባህሉን ቀይሮ ህይወቱን ከአንድ ደረጃ ወደሌላኛው እያሸጋገረ አኩሪ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ማንንም ተጠቃሚ የማያደርገው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ቅስቀሳ ሰለባ እንዳይሆን፣ ለዕውቀትና ለሥራ እጅግ ውድ የሆነውን ጊዜውን በአልባሌ እንዳያባክን፣ በተለይም እንደአገር በመዘናጋታችን የተነሳ እንደአዲስ እያገረሸ ላለው የኤችአይቪ ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ በጥብቅና በቀጣይነት መስራት ይኖርበታል። ይህንን ጥረቱን ማገዝ የወላጆችም፣ የመምህራንና የሌሎችም ባለድርሻ አካላትና የመላው ህብረተሰብ ኃላፊነት እንደሆነም ሊታወቅ ይገባዋል።

በጥፋት ኃይሎች እንቅስቃሴ ምክንያት በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር የሚደረጉት አንዳንድ እንቅፋቶች መሰረት የሌላቸው በመሆናቸው እንደወትሮው ሁሉ ይከሸፋሉ፡፡ ምክንያቱም ለዘመናት ስር የሰደደ መተሳሰብና መቻቻል ባጎለበቱ ህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር የሚደረግ የውስጥም ይሁን የውጭ የጥፋት እንቅስቃሴ የሚዘልቅ ውጤት አያመጣምና፡፡

በመሆኑም ከፊታችን የሚጠብቀንን በዓል ስናከብር በእስካሁኑ ስኬታማ ጉዟችን ያጋጠሙንን ችግሮች እየፈታን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣ በህዝቦች የጋራ ጥረት የገነባናትን አዲሲቷ ኢትዮጵያ የበለጠ ለማድመቅ ቃላችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባል፡፡