ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ከመቼውም በላቀ ተነሳሽነት እጅ ለእጅ ተያይዘን የፀረ-ድህነት ትግሉን እናፋፍም

መንግስት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። በዚሁ መሰረትም፣ መሪው ድርጅትም ብዙ ጊዜ ወስዶ ራሱን ሲያጠራ ቆይቷል፡፡ ድርጅቱ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ፣ ነፃና ግልጽ በሆነ መንገድ ዕድገታችንን ያስቀጥላል ብሎ የሚያምንበትን መሪውን መርጧል፡፡ በቀጣይም ህገ መንግሥታችን በሚፈቅደው መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ይሆናል። በአጠቃላይ ልማታዊው መንግስታችን አሁን ያለበት ጊዜ ራሱን በማረም ሂደት የአገራችንን የተሃድሶ ጉዞ ለማስቀጠል ቁርጠኝነቱን በተግባር እየገለጸ ያለበት ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍና በሂደትም ከፍተኛ ስልጣኔ ላይ ከደረሱ አገራት ጋር ለመደመር ያስቀመጠችውን ራዕይ፣ በነጠሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራች ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችውን ሁለንተናዊ ዕድገት ከቅልበሳ ለመታደግ፣ ብሎም ዕድገታችንን በተሻለ ግለት ለማስቀጠል የሚቻለው ካለፍንበት ሂደት ጠንካራውን ጎናችንን እያጎለበትን፣ ደካማ ጎናችንን ደግሞ እያረምን መሄድ ስንችል ነው። ከዚህ በመነሳትም መንግሥት እያካሄደው ያለው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የአዲሱ አመራር ውጤታማነት ሊረጋገጥ የሚችለው በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥታችን ብቃት ያለው አፈጻጸም እና በህዝባችን ንቁ ተሳትፎ እንደ አንድ አካል በጋራ ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡

በተለይም ዛሬ፣ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ወሳኝ ኃይል እና የነገ አገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱ ትውልድ በአገሩ ጉዳይ ላይ የሚጫወተው ገንቢ ሚና ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር መላው ህዝባችንም ይሁን ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል የሚያነሳቸው የልማት፣ የዴሞከራሲ፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላማችን ግንባር ቀደም ዘብ መሆን ይጠበቅበታል።

የህዝቦቹን ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ የሚገኘው ልማታዊው መንግሥታችን፣ ያጋጠሙንን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራቱን እንደሚቀጥልም በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡ አሁን የምንገኘው በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደመሆኑ ከስህተታችን እየታረምን፣ ጥንካሬዎቻችንን አያስቀጥለን እስከሄድን ድረስ ከህዝባችን ጋር ሆነን የማንፈታው አንዳችም ችግር እንደማይኖርም መንግሥት ያምናል።

የአገራችን ሕዝቦች ድህነትን ለማሸነፍ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አጠናክረው በመቀጠል በተሃድሶ ለውጥ ውስጥ እያለፈ ካለው ከልማታዊው መንግስታችን ጎን ተሰልፈው ዕድገታችንን ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ መረባረብ ይጠይቀናል፡፡

የህዝቦቻችንን እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ትክክለኛ መስመር ይዞ እየተጓዘ ያለው ልማታዊው መንግስታችን መስመሩን አስጠብቆ በማስቀጠል በላቀ የህዝብ ተሳትፎ የአገራችንን ዕድገት ወደተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

በመሆኑም፣ አሁን የምንገኝበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ተነሳሽነት እጅ ለእጅ ተያይዘን የአገራችንን ሕዳሴ የምናስቀጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ሁላችንም ተገንዝበን የፀረ-ድህነት ትግሉንን እንድናፋፍም መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡