ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ሐምሌ 21 ቀን 2009 ዓ.ም

አሳታፊነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን ተሃድሶውን እናስቀጥላለን!
የኢፌዴሪ መንግሥት በ2009 ዓ.ም መግቢያ ላይ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ በገባበት ወቅት ቁልፍ የሆኑ የአመራር ድክመቶችን እንደለየ፣ እነሱንም ማረም እንደሚገባና ይህም በሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት በሚካሄድ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ መከናወን እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ይታወሳል።
በዚሁ መሰረትም በድርጅት፣ በመንግስት እና በህዝብ ደረጃ በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮች የተካሄዱ ሲሆን በሁሉም አካላት ዘንድ በአስተሳሰብ ደረጃ ችግሮችን በውይይት ለመቅረፍና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱ የሚታወስ ነው። በመሆኑም ይህ መሰረታዊ ጉዳይ የጥልቅ ተሃድሶው የመጀመሪያ ስኬት ነበር።

በመሆኑም ለስልጣን ያለ የተሳሳተ አተያይ በጥልቅ ተሃድሶ የተለየ ዋና የአመለካከት ችግር ሲሆን በአንድ በኩል አመለካከትን በመቀየር በልማታዊ አስተሳሰብ የመተካት ሥራ በማጠናከር በሌላ በኩል የአሳታፊነትና የተጠያቂነት አሰራርን በማስፈን አጥፊዎችን ለህግ ተጠያቂ ለማድረግ ተሞክሯል። ተሃድሶ ሂደት ስለሆነ ደረጃ በደረጃ ወደተፈላጊው ውጤት እንደሚያደርስም የታመነ ነው።

እንደሚታወቀው የመንግሥት ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የመንግሥት ሃብትን ለግል ጥቅም በማዋል ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ነጋዴዎችና ደላሎች ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ይህንኑ ጉዳዩ በተመለከተ መንግሥት በየወቅቱ ለህዝብ መረጃ ይፋ ማድረጉንም የሚቀጥልበት ይሆናል።

አስፈላጊው መረጃና ማስረጃዎች እስከቀረቡ ድረስ የመንግስትንና የህዝብን ሃብትና ንብረት ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትንና የሚያውሉትን አካላት ሁሉ ያለአንዳች ርህራሄ ለፍርድ ማቅረቡን እንደሚቀጥልበት መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
በዚህ አጋጣሚ መረጃ እና ማስረጃ በመስጠትና በመጠቆም ለተባበሩ ዜጎቻችን ሁሉ የኢፌዴሪ መንግሥት ምሥጋናውን እያቀረበ ይኽው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን ያስተላልፋል።

የተጠያቂነት አሠራርን ማስፈን የማይታለፍ ተግባር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር ታግሎ በልማታዊነት ለመቀየር በሕብረተሰብ ደረጃ የሚፈጠር የአመለካከት ለውጥ ወሳኝ መሆኑን መንግሥት በጽኑ ያምናል። ይህ አገራዊ መግባባት ሊፈጠርበት የሚገባ የጋራ ጉዳይ ነው፡፡

በመሆኑም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አመለካከትን መፈተሽና የተዛባውን ማስተካከል የዜግነት ሃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ምክንያቱም ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው አገራችንን ለሙሰኞች፣ ለዘራፊዎችና ለሌቦች የማትመች ማድረግ የምንችለው፡፡ ይህንን ማድረግ ስንችልም ነው አገራችን የተያያዘችውን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ዕድገት ማስቀጠልና ማፋጠን የምንችለው፡፡ በመሆኑም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የያዘውን የበላይነት ከሥር መሰረቱ ለመናድ እና በምትኩ ልማታዊነት ሥር እንዲሰድ ለማድረግ ሁላችንም እንረባረብ!