ዜና ዜና

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በአጀንዳ 2063 መሰረት ለተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተሞክሮ ለመውሰድ ያስችላል

አፍሪካ በአጀንዳ 2063 መሰረት ለጀመረቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የፈጠረውን የመነቃቃት መንፈስና ተሞክሮ መውሰድ እንደምትፈልግ የአፍሪካ ህብረት ገለጸ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዲፕሎማሲ፣ በገንዘብ ድጋፍና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ነው።

የግድቡን ግንባታ እውን ለማድረግም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከኅብረተሰቡ ከዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል። 

የህብረቱ የስትራቴጂ፣ ፖሊሲ ፕላኒንግ፣ ቁጥጥር፣ ክትትልና የሃብት ማሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያ ህዝብ መነቃቃት፣ ተሳትፎና የአገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብ መንገድ ለሌሎች የአህጉሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አርአያ ነው።

የተቀናጀ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የባቡር ትራንስፖርት ትስስር፣ የአፍሪካ ቨርቹዋልና ኢ-ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካ የሸቀጣ ሸቀጥ ስትራቴጂና የአፍሪካ ዓመታዊ መድረክ የሚሉት ከአጀንዳ 2063 መካከል ትኩረትና ቅድሚያ የተሰጣቸው ትላልቅ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች ናቸው።

አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና መመስረት ፣የአፍሪካ ፓስፖርትና ነፃ የሰዎች ዝውውር፣ በኮንጎ ወንዝ ላይ የሚገነባው ትልቁ የኢንጋ ግድብ ፣የፓን አፍሪካ ኢ-ኔትወርክ፣ የአፍሪካ አውተር ስፔስ ስትራቴጂ ሌላው የፕሮጀክቶቹ አካላት ናቸው።

በተለይ በኮንጎ ወንዝ ላይ በ50 ቢሊዮን ዶላር በሦስት ደረጃ የሚገነባው የኢንጋ ግድብ 42 ሺ ሜጋ ዋት በማምረት የበርካታ አገሮችን የኃይል አቅርቦት እንደሚያሟላ ይጠበቃል።  

ፕሮጀክቶቹ በአህጉሩ ማህበረ-ኢኮኖሚ ልማት እንዲመጣና የዜጎች በራስ መተማመን እንዲጨምር የሚያደርጉ ናቸው።  

ይሁንና ፕሮጀክቶቹን ገንብቶ በወቅቱ ለማጠናቀቅ በተለይ የፋይናንስ ችግር እንደ ዋና ተግዳሮት የሚጠቀስ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት። 

''ይህን የፋይናንስ ችግር ለማቃለል አህጉራዊ ሃብት ማሰባሰብ ያስፈልጋል'' ያሉት አቶ መስፍን፤ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ በህዝቦቿ ተሳትፎና በራሷ አቅም ለመገንባት የተከተለችው መንገድ ለአህጉሩ ምሳሌና አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመሸጥ ዜጎች ከቦንዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የቁጠባ ባህላቸው እንዲያድግና የፕሮጀክቱ ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል።    

በአፍሪካም ለሚገነቡት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከውጭ በሚገኝ የገንዘብ እርዳታና ድጋፍ ላይ የሚደረግን ጥገኝነት ያስቀራል። 

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቀድሞ  ዋና ፀሃፊ ኬፕታውን ዩንቨርሲቲ ምሁር ፕሮፌሰር ካርሎስ ሎፔዝ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ የሆነውን ግድብ ለመገንባት አገራዊ ሃብት የማሰባሰብ ሂደት፣ የቁጠባ ባህልና ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎን ተጠቅማለች።

ይህ ደግሞ በርካታ አገሮች ትላልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በተመሳሳይ መንገድ እንዲገነቡ መነቃቃት እንደሚፈጥረ ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ጀምሮ፣ ዲያስፖራውንና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ አገራዊ ሃብትን መሰብሰቧ "ሌሎች አገሮችንም እያነሳሳ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።  

አጀንዳ  2063 በዋናነት 20 ግቦች፣ 37 የተመረጡ ክንውኖች፣ 7 ራዕዮችና 13 ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያቀፈ የግማሽ ክፍለ ዘመን እቅድ ነው።

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2009 /ኢዜአ/