ዜና ዜና

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በ2009 110 ሚሊየን ብር ማግኘቱን ገለጸ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ከ110 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ በከተማው ባሉት ሁለት መስመሮች ከ35 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን ማጓጓዝ በመጓጓዝ ከ110 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡
ገቢውና የአገልግሎት አሰጣጡ ከዕቅዱ አንፃር የታለመውን ግብ ለማሳከት አልተቻለም ብለዋል ፡፡

የዚሁ ምክንያትም የኃይል መቆራረጥ፣ የመለዋወጫ መሳሪያዎች አቅርቦት እጥረት፣ የግንኙነት ገመዶች መቆራረጥ እና የባቡሮች ዓመታዊ ፍተሻ መግባት በዋና መሆናቸውን ነው ያመለከቱት ፡፡

ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ ትርፋማ መሆን ባለመቻሉ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየዓመቱ ከሚደረግለት የ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ድጎማ ባሻገር በከተማዋ በተመረጡ አስር ቦታዎች ላይ ተጨማር የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለማከናወን ከከተማ አስተዳዳሩ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደዚሁም ችግሩን ለመፍታት ባቡሩን የማስተዳደር ሥራዎችን ከቻይናው ኩባንያ በመጪው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ለመረከብ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል ፡፡
የባቡር ሹፌሮች፣ ኢንጂነሮችና ሌሎች ተጨማሪ የሰው ኃይል በማሰልጠን ረገድ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ደረጄ አብራርተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከመስከረም 9/2009 ዓመተ ምህረት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ65 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንደተቻለም መግለጻቸውን ዋልታ ዘግቧል፡፡

ነሀሴ 5/2009