ዜና ዜና

ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ለሕዳሴው ግድብ 200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረጉ

 

 

 

 

 

 

 

 

በምስራቅ ጎጃም ዞን ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

አርሶአደሮቹ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 200 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ታውቋል።

የስናን ወረዳ የጠድ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አናጋው ላመስግን ለኢዜአ እንደተናገሩት እስካሁን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከ8 ሺህ ብር በላይ ቦንድ ግዥ ፈጽመዋል።

ግድቡን በአካል ሄደው ማየታቸውና ግድቡ ሲጠናቀቅ ለሀገር ያለውን ጠቀሜታ በመረዳታቸው በየዓመቱ ከ1 ሺህ እስከ 2 ሺህ ብር ድጋፍ ለግንባታው እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

በቀጣይም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በአዋበል ወረዳ የለኩማ ሀሬራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አብተው ደጀኔ በበኩላቸው፣ በዓመት ከሚያገኙት ገቢ እስከ 3 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት አቅደው ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሰሞኑንም የ1 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን ነው የገለጹት።

የግድቡ ግንባታ ለሀገር ልማት የሚፈጥረውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ከ25 ሺህ ብር በላይ ቦንድ ገዝቺያለሁ " ያሉት ደግሞ በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የደንባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አያሌው አጤ ናቸው ።

የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል ለራሳቸው ቃል መግባታቸውንም ተናግረዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የህዝብና ሚዲያ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጋሻየ ጌታሁን እንዳሉት ግንባር ቀደም አርሶ አደሮቹ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በመሪነት ከመሰማራት ባለፈ ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው።

አርሶአደሮቹ ለሕዳሴው ግድብ ግንባር ቀዳሚ በመሆንና ለሌሎችም አርአያ ለመሆን ባደረጉት ጥረት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ200 ሺህ ብር የቦንድ ግዢ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ከእዚህ ቀደም ከየወረዳው የተውጣጡ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ግድቡን በመጎብኘት ቦንድ የሚገዙበትን የገንዘብ መጠን የማሳደግና የአካባቢያቸውን  አርሶ አደሮች  ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎችን በማከናወን እገዛ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የግደቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ከዞኑ  ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥ እና በስጦታ ድጋፍ መደረጉን ቡድን መሪው አስረድተዋል።

ደብረ ማርቆስ መጋቢት 2/2010/ኢዜአ