ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ ታህሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም

የታላቋ አገራችን ሰላምና ልማት በታላቁ  ህዝባችን ባለቤትነት ይጠበቃል!

የአገራችን ሕዝቦች በጋራ ተስማምተው ባፀደቁት ሕገ - መንግስት መተዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ አስተማማኝ ዴሞክራሲና ፈጣን ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት ረጅም የስኬት ጉዞ አሳልፋለች።

አገራችን በውጪው ዓለም ዘንድ ለረጂም ዘመናት ስትታወቅበት የነበረው ድርቅና ረሃብ ተፈጥሮአዊ ክስተት ሆኖ በየጊዜው መምጣቱ ባይቀርም ከእንግዲህ ለህዝባችን አደጋ የማይሆንበትን ውስጣዊ አቅም ማጎልበት በመቻላችን የማንንም እጅ ሳንጠብቅ በራሳችን አቅም መቋቋም የቻልንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

እንዲያውም ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ  የምትታወቀው በረሃብ መሆኑ አብቅቶ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ሆኗል፡፡

 ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች "የአፍሪካ ነብር"፣ "የአፍሪካ አንበሳ"፣ "አዲሲቷ ቻይና" ወዘተ የሚል ቅጽል ሥም ለአገራችን መስጠታቸው የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡

 በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተመራጭ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል እንደምትሆንም ከወዲሁ እየመሰከሩልን ያሉት ብዙዎች ናቸው።

 ከ10 እና 15 ዓመታት በፊት አንዲት ቅንጣቢ አበባ ወደ ውጭ ልካ የማታውቀው አገራችን ዛሬ በዓለም ዋነኛ ተፎካካሪ ሆናለች።

በኃይል ማመንጨት ዘርፍም እየገነባናቸው ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምናደርገውን ሽግግር ከማፋጠንና ከሌሎች በርካታ ታላላቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ባሻገር በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ለሌሎቹ ሀገራት ተምሳሌት እየሆኑ ይገኛል።

 ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በሰባት ዓመታት ውስጥ የመብራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ''ብርሃን ለሁሉም'' የተባለ መርኃ ግብር ዘርግተን ተግባራዊ ማድረግ መጀመራችንም አገራችን ወዴት እያመራች መሆኗን የሚመሰክርልን ነው። በእርግጥም ታላቅ አገር እየሆንን ለመምጣታችን ተዘርዝረው የማያልቁ ሌሎች ስኬቶችን መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ እስካሁን በመጣንበት ሂደት ያስመዘገብናቸው ድሎች እጅግ በርካታ የመሆናቸውን ያህል በየጊዜው ያጋጠሙን ልዩ ልዩ ፈተናዎች እንደነበሩም ይታወቃል፡፡

የሚያጋጥሙንን ችግሮች ሁሉ ግን መንግስትና ሕዝብ በተቀናጀ መንገድ መንገድ እየፈታን ለተደማሪ እድገት በግብዓትነት እንዲውሉ እያደረግን መጥተናል። በዚህም የእድገታችንን ቀጣይነት ማረጋገጥ ችለናል። ከዚህ አንጻር፣ አሁንም ያልተሻገርናቸውን አንዳንድ ችግሮች ባለፍንበት መንገድ ለተደማሪ እድገት ግብዓት እንደምናውላቸው አንዳችም ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም፡፡

በአጠቃላይ አገራችን ታላቅ መሆን የጀመረችው ከምንም በላይ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈኗ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

 ሁከት፣ ብጥብጥና ግጭት ባለበት ሁኔታ አስተማማኝ ዴሞክራሲ አሊያም ፈጣን እድገት ሊታሰብ አይችልምና! ግጭት ወደ ድህነት አዙሪት የሚመልስ፣ አሊያም የድህነት እድሜን የሚያራዝም፣ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረውን ትግል የሚያደናቅፍ ተግባር በመሆኑ ሁላችንም ልንከላከለው ይገባል፡፡

 በአንጻሩ ሰላምን መጠበቅ የልማታችንና የብልጽግናችን ብቻ ሳይሆን የህልውናችን መሰረት መሆኑንም በውል ልናጤነውና ልንንከባከበው ይገባል፡፡

በመሆኑም፣ መላው ሕዝባችን ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸውን የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የመደጋገፍ፣ ችግሮች ሲጋጥሙም በመነጋገር የመፍታት እሴቶቹን አጠናክሮ በመቀጠልና ለወጣቱ ትውልድም በማስተላለፍ ሰላማችንን አስተማማኝ እንድናደርግ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

የመጣንበትን የከፍታ ጉዞ ማስቀጠል፣ ታላቅ አገር የመመስረት ራዕያችንንም ማሳካት የምንችለው በቅድሚያ ሰላማችንን በመጠበቅ ችግሮቻችንን በጋራ ውይይት እየፈታን መሄድ ስንችል በመሆኑ ለሰላማችን ሁሉም ዜጋ ዘብ ይቁም!