ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ - ሚያዚያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም

ለተሟላ የዜጎች ህገ መንግሥታዊ መብቶች መከበር እንረባረብ!
ሀገራችን ሁለተኛውን ብሄራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ሰሞኑን ይፋ አድርጋለች፡፡ የዜጎችን የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች መብቶች በተሟላ መልኩ መተግበራቸውን ለማረጋገጥ ታቅዶ ለ2ኛ ጊዜ የወጣው የድርጊት መርሃ ግብር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡ የድርጊት መርሃ ግብሩ ከአሁን በፊት ተቋማት በተናጠል ይፈጽሙት የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ስራ አስፈጻሚዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የብዙሃን ማህበራትና በዘርፉ የተሰማሩ አለም አቀፍ ተቋማት በተቀናጀ መንገድ እንዲያከናውኑት እድል የሚሰጥ ነው። በመሆኑም የዜጎችን የሰብዓዊ መብቶች ከማረጋገጥ አኳያ ተጨማሪ ሃይል የሚፈጥር ይሆናል።

ህገ-መንግስቱን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይበልጥ እንዲረጋገጡ ለማድረግ በሚያግዝ መልኩ ታቅዶበት የወጣው ይህ መርሃ-ግብር፡ መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ፡ በዚህም አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና የዳበረ ዴሞክራሲ ሥርዓት በአገራችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

እንደሚታወቀው አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተመራችበት ያለው ህገ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎችን ያካተተ፣ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳትም ዴሞክራሲና ልማት የማይነጣጠሉ የአገራችን የህልውና መሰረት መሆናቸውን በግልጽ የተቀበለ ተራማጅ ህገመንግስት ነው። በዚህ ወርቃማ ህገ መንግሥት እየተመራንም ላለፉት 15 ዓመታት ባሳለፍነው ሂደት በበርካታ አዳጊ ሀገራት ዘንድ ተምሳሌት ተደርገው የተወሰዱ አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ ችለናል።

እንደዚያም ሆኖ በስኬቶቻችን ከመኩራት ይልቅ ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችንን በመፈተሽ ያስመዘገብናቸውን ውጤቶች በተሻለ ጥራት ለማስቀጠልና ድክመቶቻችንን ለማረም ሲባል ከዚህ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናችን ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን ሥር እንዲሰድ ለማድረግ መንግሥት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከሲቪል ማህበራት፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየመከረ ይገኛል። በሂደቱም ለነገ የበለጠ አገራዊ ስኬት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ባለበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

የኢፌዴሪ መንግስት፡ ሁለተኛው ብሄራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር አገራችን እያካሄደችው ያለው የተሃድሶ እንቅስቃሴ አካል በመሆኑ፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ከመንግሥት ጎን ቆመው እንዲረባረቡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡