ዜና ዜና

አገር አቀፍ የሲሚንቶ ፍኖተ ካርታ በ2010 በጀት ዓመት ተግባራዊ ይሆናል

በአገር አቀፍ ደረጃ  የሲሚንቶ ፍላጎትን ለማሟላት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 በኬሚካል ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩትና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው "የሲሚንቶ ፍኖተ ካርታ" በማምረት ሒደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ነው ።

 እ.ኤ.አ እስከ 2025 የሚያገለግለው ፍኖተ ካርታ ሲሚንቶ ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የሚያግዙ ተሞክሮዎችን መያዙንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

 የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፍኖተ ካርታው አገሪቷ በየወቅቱ የሚያስፈልጋትን የምርት መጠን የሚያሳይ ነው።

 አገሪቱ ሲሚንቶ ለማምረት ከሚያስፈልጋት የሃይል ፍጆታ ውስጥ ከ40 እስክ 60 በመቶ የሚሸፈነው በድንጋይ ከሰል  በመሆኑ ለዚህም  የውጭ ምንዛሪ እንደምታወጣ  ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

 ''ይህም ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ የኢትዮጵያ የሲሚንቶ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓታል'' ብለዋል።

 የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሙያዎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢራንን የሲሚንቶ አመራረት ተሞክሮ ቀስመው መመለሳቸውን  ዶክተር ዓለሙ ገልጸዋል።

 ኢራን ላይ የአንድ ቶን/10 ኩንታል/ የሲሚንቶ ዋጋ ከ 25 እስከ 30 ዶላር እንደሚደርስ የተናገሩት ዶክተር ዓለሙ በኢትዮጵያ የአንድ ኩንታል የሲሚንቶ ዋጋ 90 ዶላር መሆኑን አስታውቀዋል።

 በኢትዮጵያና በኢራን የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዋናነት ያለው ልዩነት የኃይል አጠቃቀም  መሆኑን ጠቁመው ''የኢራንን የሃይል አጠቃቀም ልምድ ብንወስድ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንችላለን'' ብለዋል።

 ኢራን ለሃይል አጠቃቀም እና ለአካባቢ ጥበቃ የምትጠቀምባቸው ቴክኖለጂዎች ከኢትዮጵያ የተሻሉ መሆናቸውን የግብረ ሃይሉ ሪፖርት እንደሚያመለክት ጠቅሰዋል።

 ኢትዮጵያ የኢራንን ተሞክሮ በመውሰድ የሲሚንቶ ምርቶቿን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንድትችል የሚያግዝ ጥናት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

 ''ፍኖተ ካርታውን መሰረት ያደረገ ጥናት በማካሄድ እየጨመረ የመጣውን የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ምርቱን ለአጎራባች አገራት ማቅረብ እንችላለን'' ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅት ለሲሚንቶ ምርት የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰል ከውጭ አገር እየገባ መሆኑን የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሀዱሾም ጥዑም አስታውቀዋል።

 ፍኖተ ካርታው በአገር ውስጥ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሲሚንቶ ለማምረት ብቁ እንዲሆን በማድረግ ከውጭ የሚገባውን ግብአት ለማስቀረት የሚያስችል አቅጣጫን አስቀምጧል።

 በሲሚንቶ ማምረት ስራ በብዛት እየተሳተፉ የሚገኙት የውጭ ባለሙያዎች የዕውቀትና  የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ ማስቻልና የሲሚንቶ  ኢንዱስትሪው በአገር ውስጥ ባለሙያ እንዲመራ ማድረግ የፍኖተ ካርታው አካል መሆኑንም አስረድተዋል።

 ፍኖተ ካርታው ከሲሚንቶ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ለሌላ ጥቅም ለማዋል የሚያስችሉ ሀሳቦችን እንደያዘና በ2010 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

 ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም  የኮንስትራክሽን ግብዓት ምርቶችን ወደ ጎረቤት አገራት በመላክ ከዘርፉ  42 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳ 19 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ብልጫ ሲኖረው ከዚህ ውስጥ 17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ከሲሚንቶ ምርት የተገኘ ነው፡፡

አዲስ አበባ  ነሐሴ 5/2009/ኢዜአ/